አምስቱ የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ጎዳናዎች በ2018

Ethiopian woman looking at phone Image copyright Getty Images

ስህተት አልባ የመሬት ምዝገባ

Image copyright AFP

በአፍሪካ አብዛኛውን ጊዜ ማስረጃዎች በአግባቡ ስለማይያዙ የመሬት ይዞታ ጉዳይ ሁሌም ያጋጫል።አሉ ተብለው የሚቀርቡ ማስረጃዎችም ብዙ ጊዜ የተሳሳቱ ሆነው ይገኛሉ።ነገር ግን የማይሰረዝና የማይሳሳት ማስረጃ ብሎክቼን በተሰኘ መንገድ ሊዘጋጅ ይችላል።ብሎክቼን መሬትን የሚመለከቱ መረጃዎች የሚደራጅበት ዲጂታል አሰራር ነው።ይህ በብሎክቼን የተደራጀ መረጃ ደግሞ በጥቂት ኮምፒውተሮች ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሺዎች ወደ ሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች የሚላክ ነው።ከዚህ አሰራር ጋር ግንኙነት ያለው ኮምፒውተር ሁሉ በየጊዜው የተሻሻለ መረጃ ይደርሰዋል።ስለዚህ አሰራሩ ግልፅና ተአማኒነት ያለው ነው።ይህን ቴክኖሎጂ በሩዋንዳ ተግባራዊ የሚያደርገው ዋይዝኪ የተሰኘ የመረጃ መረብ ደህንነት ኩባንያ ነው።እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ላይ የሩዋንዳ መንግስትን የብሎክቼን ተጠቃሚ ለማድረግ ከማይክሮሶፍት ጋር መፈራረሙን ዋይዝኪ አስታውቋል።የመጀመሪያው እርምጃ በሩዋንዳ የመሬት ምዝገባና ስነዳን ዲጅታላይዝ ማድረግ ነው።ኩባንያው በሩዋንዳ የብሎክቼን ማእከል ያቋቋመ ሲሆን በ2018 እንደ ቢትኮይን የሩዋንዳን ክሪፕቶከረንሲ(ምናባዊ የኢንተርኔት መገበያያ)ለመስራት እቅድ አለው።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎችን ለአፍሪካ ማስተላለፍ

Image copyright Getty Images

አለም የሶፍትዌር ሰሪዎች እጥረት አለባት።በሌላ በኩል አፍሪካ ደግሞ በወጣት ህዝብ የተሞላች ነች።አሜሪካና አውሮፓ አፍሪካዊ ሶፍትዌር ሰሪዎችን ቢያሰለጥኑ በዚህ የሰው ሃይል ይጠቀማሉ።አንዲላ ሶፍትዌር ሰሪዎችን ናይጄሪያ ውስጥ አሰልጥኖ በአለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያስቀጥር ኩባንያ ነው።በዚህ መልኩ አንዲላ እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት ያሰለጠናቸውን በማስቀጠር 40 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።በ2016 ደግሞ ከፌስቡኩ ማርክ ዙከርበርግ 24 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።በ2018 ደግሞ አንዲላ በግብፅም ማዕከል እንደሚከፍት ይጠበቃል።

ማንኛውንም ክፍያ ቀላል ማድረግ

Image copyright Getty Images

በአፍሪካ ብዙ ሰዎች የባንክ ሂሳብ የላቸውም።በሌላ በኩል የሞባይል ክፍያ ስርአት ውጤታማ እንደሆነ ታይቷል።በጥናት እንደታየው አፍሪካ መቶ ሚሊዮን ሰዎች የሞባይል የገንዘብ ሂሳብ የከፈቱባት አህጉር በመሆን አለምን ከሚመሩ ተርታ ተሰልፋለች።በአሁኑ ወቅት የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎት ብድርና ቁጠባን፣መድህንንና ሃዋላን ያካትታል።ችግሩ በዚህ መልኩ የሚሰሩ ስርአቶች በርካታ መሆናቸውና አንድላይ አለመስራታቸው ነው።ይህ ማለት ደግሞ አፍሪካ ውስጥ እቃዎችን በኢንተርኔት መግዛት አለመቻል ነው።ለምሳሌ ፍለተርዌቭ የተባለው ስርአት በመላ አፍሪካ ለባንኮችና ለሌሎች ኩባንያዎችም የሞባይል ክፍያ ስርአት ዝርጋታን እውን አድርጓል።በአውሮፓውያኑ 2017 የመጀበሪያው ሶስት ወር ውስጥ ፍለተርዌቭ 444 ሚሊዮን ዶላር በናይጄሪያ፣ጋናና ኬንያ አዘዋውሯል።ከመጀበሪያው ጀምሮ ኩባንያው በአስር ሚሊዮን ዝውውሮች 1.2 ቢሊዮን ዶላር አስተላልፏል።በዚያው ዓመት ኩባንያው ከአሜሪካ የአስር ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝቷል።ይህ ድጋፍ ለኩባንያው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርለት የሚጠበቅ ሲሆን በአፍሪካ ሰዎች በኢንተርኔት በቀላሉ የፈለጉትን መግዛት የሚችሉበትን ስርዓት እንደሚዘረጋ ይጠበቃል።

በድሮን መልዕክት ማድረስ

Image copyright Reuters

አለም ላይ በድሮን አነስተኛ ነገሮችን ከቦታ ወደ ቦታ የማመላለስ አገልግሎት የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት አለ።በርግጥ በአቬሽን ህግ ምክንያት ይህ በአሜሪካና በአውሮፓ ተከልክሏል።በተወሰኑ የአፍሪካ አገራት ለምሳሌ በሩዋንዳ ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል።የገጠር መንገዶች ምቹ አለመሆንና የበረራዎች ሰፊ ቦታዎችን አለመሸፈን ለድሮን መልዕክት አገልግሎት አፍሪካን ምቹ ያደርጋታል።ዚፕላየን የተሰኘው ኩባንያ እንደ ደም፣ክትባትና ሌሎች መድሃኒቶችን አይነት ቀላል ነገሮችን የሚያደርሱ ድሮኖች አሉት።የአለም የመጀመሪያው የድሮኖች ወደብ የተከፈተው እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በሩዋንዳ ነበር።በወቅቱ ወደቡ በታንዛኒያም እንደሚከፈት ተገልፆ ነበር።በ2018 የታንዛኒያው ዶዶማ ድሮን ወደብ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።በአብዛኛው የሚያመላልሰውም መድሃኒት ነክ ነገሮችን ይሆናል።ፎርብስ እንዳለው ይህ በአለም ትልቁ የድሮን መልዕክት ማድረስ ስርአት ይሆናል።

ያለ ኤሌክትሪክ ሃይል ማሰራጫዎች መብራት እንዲኖር ማድረግ

ፔግ አፍሪካ ከኤሌክትሪክ ማሰራጫዎች ሃይል ለማይደርሳቸው ሶላር ፓኔሎችን የሚሸጥ ድርጅት ነው።ሶላር ፓኔል መግዛት ለብዙዎች ውድ በመሆኑ ሰዎች በአነስተኛ የሞባይል ክፍያዎች ኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታም ኩባንያው አመቻችቷል።በዚህ መልኩ እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ላይ ፔግ 13.5 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።ፔግ አፍሪካ በጋናና በአይቮሪኮስት እየተስፋፋ ነው።