የካሊፎርኒያ መሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የካሊፎርኒያ መሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው Image copyright SANTA BARBARA NEWS VIA REUTERS

የካሊፎርኒያ የመሬት መንሸራተት እስካሁን የ17 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን አሁንም በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በፍርስራሽ ውስጥ እንዳሉ እየተዘገበ ይገኛል።

ሳንታ ባርብራ በተሰኘው ወረዳ 28 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካቢቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ከ100 በላይ መኖሪያ ቤቶች ከጥቅም ውጭ ሲሆኑ ሌሎች 300 የሚሆኑት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በርክሊ ጆንሰን የተባለ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ አንዲት የሁለት ዓመት ህፃን ከፍርስራሽ ስር በሕይወት ብትገኝም ከባድ አደጋ ስለደረሰባት ወደ ሕክምና መስጫ ቦታ መወሰዷን ተናግሯል።

"በሕይወት መገኘቷ በራሱ ለእኔ ተዓምር ነው" ሲል እንባ የተናነቀው በርክሊ ለሳንታ ባርብራ ጋዜጠኞች ተናግሯል። አክሎም የገዛ ቤቱ ከጥቅም ውጪ እንደሆነና ከባለቤቱ ጋር በመሆን ህፃን ልጃቸው ሊያድኑ እንደቻሉ አሳውቋል።

የወረዳዋ ጥበቃ ኃላፊ ቢል ብራውን እንዳሳወቁት ምንም እንኳ 50 የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት መታደግ ቢቻልም 13 ሰዎች የት ይግቡ የት ምን ዓይነት ፍንጭ የለም።

Image copyright EPA

መሬት መንሸራተቱ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባት የካሊፎርንያ ግዛት ደቡባዊ ክፍል ታዋቂ አሜሪካውያን ለመኖሪያነት የሚመርጧት ናት።

ከእነዚህም መካከል የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢዋ ኤሌን ዲጀነረስ እና አፍሪካ-አሜሪካዊቷ የሚድያ ሴት ኦፕራ ዊንፍሬይ ይገኙበታል።

ባለፈው ወር በካሊፎርንያ ግዛት የደረሰው ሰደድ እሣት መሬቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት አሁን የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ለመሬት መንሸራተቱ እንዳጋለጠ ባለሙያዎቹ እየዘገቡ ይገኛሉ።

የአሜሪካ አደጋ ጊዜ መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው አካባቢው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመሰል አደጋዎች የተጋለጠ ነው።

በመሬት መንሸራተቱ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የካሊፎርንያ ግዛት ነዋሪዎች አካባቢውን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ