ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን ማገድ አዋጭ ነው?

አሻንጉሊት የያዘች ህፃን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት የውጭ ጉዲፈቻን የሚያግድ አዋጅ አፅድቋል። የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ ቀጣዩ እርምጃ ምን ይሆናል? እገዳውስ የሚያዋጣ አካሄድ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ከዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በጉዲፈቻ ወደ ተለያዩ አገራት የሚሄዱ ህፃናት ለማንነት ቀውስና ለተለያዩ ጉዳቶች እየተጋለጡ በመሆናቸው እንደሆነ መንግሥት ገልጿል።

ችግሩ በጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገራት ከሄዱ በኋላ የህፃናቱ ለማንነት ቀውስ መጋለጥ ብቻም ሳይሆን የሚሄዱበት መንገድም በብዙ ችግሮች የተሞላ መሆኑ ነው።

የውጭ አገር ጉዲፈቻ ለብዙ ተቋማትና ግለሰቦች ትልቅ የገቢ ምንጭ ሆኖ ነበር። ልጆች የተሻለ ህይወት ይኖራቸዋል በሚል የሀሰት ተስፋ ወላጆችን አታሎ ህፃናትን በጉዲፈቻ መላክን ሥራቸው ያደረጉ ደላሎችና ኤጀንሲዎችም በርካታ ነበሩ።

ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የተሰለፉ ወላጆችም ነበሩ።

በዚህ መልኩ ከኢትዮጵያ ይወሰዱ የነበሩ ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ነበር። በአንድ ወቅት በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉዲፈቻ ከሚሄዱ ህፃናት አንድ አራተኛ የሚሆኑት ከኢትዮጵያ የሚወሰዱ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ብዙዎች ለትርፍ ተሰማርተውበት የነበረው ይህ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ የተለያዩ የውጪ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረትም ስቦ ነበር።

ህገ-ወጥና ህጋዊ አሰራሮች ተደበላልቀው ህፃናት በገፍ ወደ ውጭ ሃገር የመላካቸው ነገር 'የኢትዮጵያ አዲሱ የወጪ ንግድ ዘርፍ' እስከመባል ደርሶ እንደነበርም ይታወሳል።

ከዓመታት በፊትም መንግሥት የውጭ አገር ጉዲፈቻን 90 በመቶ እንደሚቀንስ አስታውቆ ነበር። በአሜሪካ አሳዳጊዎች ተወስዳ በረሃብና በስቃይ የሞተችው የ13 ዓመቷ ሃና አለሙ ታሪክ ደግሞ የውጭ ጉዲፈቻ በምን ያህል ደረጃ ህፃናትን ለስቃይ እየዳረገ እንደሆነ ማሳያ ሆነ።

ይህን ተከትሎም መንግሥት በርካታ የጉዲፈቻ ኤጀንሲዎችን ዘጋ። ከዓመታት በኋላም አሁን የፀደቀው የክልከላ አዋጅ ረቂቅም መጣ።

ቢሆንም ግን በጉዲፈቻ ወደ ውጭ የሚሄዱ ህፃናት ሁሉ ለችግር ይጋለጣሉ ማለት አይቻልም። ይልቁንም የተሻለ ህይወትና እድል የሚያጋጥማቸው በርካቶች ናቸው።

የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ

ሦስት ልጆች ወልደዋል። ነገር ግን ከአስራ ሦስት አመታት በፊት መንገድ ላይ ያገኟትን የአራት ቀን ህፃን አራተኛ ልጃቸው አድርገው እያሳደጉ ነው። ይህች ልጃቸው ስለማንነቷ የምታውቀው ነገር ስለሌለ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም። በወቅቱ የህፃኗ እናት በተወሰነ መልኩ አዕምሮዋ ትክክል ስላልነበር ህፃኗን ትቶ ማለፍ አልቻሉም።

"ህፃኗን በዚያ ሁኔት ብንተዋት በጥቂት ቀን ውስጥ ትሞት ነበር" ይላሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የትም ቦታ ቢኬድ ችግረኛ ህፃናት አሉ። ጥሩ ኑሮ ያላቸው በርካታ ሰዎች ግን ምናልባትም እነዚህን ህፃናት አንድ ጊዜ መርዳት እንጂ ወስደው እንደማያሳድጉ ይናገራሉ። ይህ የእሳቸው አስተያየት ብቻም ሳይሆን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።

"ምንም እንኳን ጉዲፈቻ ከጥንት ባህላችን ነው ቢባልም፤ ሁሉ የሞላላቸው እንኳ ልጅ ሲያሳድጉ አይታይም" በማለት ያስረግጣሉ።በጉዲፈቻ ልጅ የሚያሳድግ የሚያውቁት አንድ ሰው ብቻ እንደሆነም ይናገራሉ።

መንገድ ላይ ያገኟትን ህፃን በጉዲፈቻ ለማሳደግ ያለፉበት የህግ ሂደት ቀና የነበረ ቢሆንም መንግሥት የአገር ውጥ ጉዲፈቻን በሚገባ አስተዋውቆታል ብለው ግን አያምኑም።

"በስፋት ካልተዋወቀ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ አለ ቢባል ምን ይጠቅማለ? ማነው ስለዚህ የሚያውቀው?" ሲሉም ይጠይቃሉ።መንግሥት ከዓመታት በፊት ጀምሮ መስፋፋት ያለበት የአገር ውጥ ጉዲፈቻ ነው፤ በዚህ ረገድም የግንዛቤ መፍጠር ስራ እየሰራሁ ነው ቢልም ዛሬም እንደ እሳቸው ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው።

ብዙዎቹ የጉዲፈቻ ኤጀንሲዎች በመዘጋታቸው ደስተኛ ቢሆኑም፤ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ የውጪ ጉዲፈቻን እንዲቀር ማድረጉ ላይ ግን አይስማሙም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጊዜው አሁን ነው?

ችግር ላይ ያሉ ህፃናትን ለመርዳት የውጭ አገር ጉዲፈቻ የመጨረሻው የማራጭ እንደሆነ መንግሥት ሁሌም ቢናገርም በውጭ ጉዲፈቻ የሄዱ ህፃናት ቁጥር ደግሞ የሚናገረው ተቃራኒውን ነው።

በህፃናትና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የህግ ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ ደረጀ ተክይበሉ የአገሪቱን የህፃናት ፖሊሲ በመጥቀስ፤ ቀጣዩ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ እረምጃ የሚያተኩረው የማህበረሰብ ድጋፍ፣ የአገር ውስጥ ጊዲፈቻና የአደራ ቤተሰብ ላይ መሆኑን ይናገራሉ።

ከተቻለ ልጆች በቅርብ ዘመዶቻቸው ባሉበትና በሚያውቁት ማህበረሰብ እንዲያድጉ ይደረጋል። ይህ ካልሆነ በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲያድጉ ይመቻቻል። በአገር ውስጥ ተቋም (በህፃናት ማሳደጊያ) እንዲያድጉ ማድረግ ደግሞ የመጨረሻው አማራጭ ነው።

ቀደም ሲል በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድም ወደ ውጭ ይሄዱ የነበሩ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም በተለይም ከ2007 ዓ.ም ወዲህ በዓመት ከአራት መቶ የሚበልጥ እንዳልሆነ አቶ ደረጀ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ክልሎች ቁጥሩን በመቀነስ ቀድመው የውጭ ጉዲፈቻን ማቆማቸውንም ይናገራሉ። "ከህብረተሰቡ ግንዛቤ፣ ልጆች ለመውሰድ ከሚመዘገቡ ወላጆች ቁጥር አንፃርም የውጭ ጉዲፈቻን አቁሞ በዚያ ሲሄዱ የነበሩ ሦስትና አራት መቶ ልጆችን አገር ውስጥ ማስቀረት ቀላል ነው" ይላሉ አቶ ደረጀ።

ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ችግሩን በአገር ውስጥ አማራጭ ብቻ መፍታት አይቻልም የሚል አስተያየት ያላቸውም አሉ።

ከዚህ ባለፈም ውሳኔው የህፃናትን በተሻለ ሁኔታ የማደግ መብትን የሚጋፋ ነው የሚል ሃሳብ ያላቸው አልታጡም።አቶ ደረጀ ደግሞ የአገሪቱ ህግ (የቤተሰብ ህግ) ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ ስለሚመለከት ውሳኔው ትክክል መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ።

"ህጉ ታሳቢ የሚያደርገው የህፃናት ጥቅምና ደህንነት ማስቀደምን ነው። ህፃናት ደግሞ በአገራቸው፣ በባህላቻውና በሚያውቁት ማህበረሰብ ውስጥ ማደጋቸው ነው ጠቃሚ ተደርጎ የሚታሰበው።"

ህፃናትን በአገር ውስጥ ለማሳደግ የተመዘገቡ ወላጆች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ መተማመን እንደሚቻልም አቶ ደረጀ ያስረግጣሉ።

አቶ ደረጀ እንደሚያስታውሱት በ2001 እና 2002 ዓ.ም ላይ በዓመት አምስት ሺህ የሚሆኑ ህፃናት ወደ ውጪ ይሄዱ ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ቁጥሩ ወደ ሦስትና አራት መቶ ወርዷል።

በአንፃሩ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻስ ባለፉት ዓመታት እየጨመረ ነው? የሚል ጥያቄ ለአቶ ደረጀ ቀርቦላቸው የነበር ቢሆንም መረጃው ከክልሎች ያልተሰበሰበ በመሆኑ ለጥያቄው መልስ ማግኘት አልተቻለም።

መዝጋት ወይስ ቁጥጥር ማድረግ?

በአገሪቱ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ችግሩን በአገር ውስጥ አማራጮች ብቻ መፍታት አዋጭ እንዳልሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሻልወርክ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶ/ር አሸናፊ ሃጎስ ይናገራሉ።

ይልቁንም ለእርሳቸው እርምጃው መንግሥት በአቅም ውስንነት ወይም ባለመቻል ከቁጥጥሩ ውጭ የሆነበትን የውጭ ጉዲፈቻ ለማቆም የወሰደው ነው።

ስለዚህም የህፃናት ደህንነትና ጥቅምን የሚያረጋግጥ ቁጥጥር ማድረግ ወይስ ሙሉ በሙሉ መዝጋት ያስኬዳል? ሲሉ ይጠይቃሉ።

"ለችግሩ መፍትሄ መሆን ያለበት የውጪ ጉዲፈቻን መዝጋት ነው የሚለው አያስማማኝም። ተገቢ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ ነው ትክክለኛው ነገር።"

በአገሪቱ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን በተቃራኒው በአገር ውስጥ ልጆችን ወስዶ የማሳደግ ልምድ እምብዛም እንደሆነ የሚያመለክቱ ጥናቶች መኖራቸውን ዶ/ር አሸናፊ ይናገራሉ።

ከዘህ በመነሳት ይህን ከፍተኛ ቁጥር በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ለመሸፈን ማሰብ "ደፍሬ ልበለው በህፃናት ላይ መፍረድ ነው" ይላሉ።