ካለሁበት 18፡ አውስትራሊያ መጥቼ እርቃናቸውን የሚሄዱ ሰዎችን ሳይ በጣም ደነገጥኩኝ

የፎቶው ባለመብት, Qananitu G Butucha
ስሜ ቀነኒቱ ቡቱቻ ይባላል ላለፉት 17 ዓመታት እዚህ በአውስትራሊያ ሃገር በሜልበርን ከተማ ነው የምኖረው።
ወደዚህ ሃገር ከመጣሁ በኋላ ትምህርቴን አጠናቅቄ በነርስነት እየሠራሁ እገኛለሁ። ከዚህ ሙያ በተጨማሪ የጋብቻ ሥነ-ሥርዓቶችን በማዘጋጀት ተጨማሪ ገቢ እያገኘሁበት ነው።
ወደዚህ ሃገር አመጣጤ ታሪክ ረዥም ነው። ባጠቃለይ ከኢትዮጵያ እንድወጣ የገፋፋኝ በሕዝቤ ላይ ከሚደርሰው ስቃይ በተጨማሪ ለፍቅር ነበር። እ.አ.አ በ1992 ያኔ ፍቅረኛዬ የነበረው ባለቤቴ ሲደርስበት በነበረው መከራ ምክንያት ወደ ኬንያ ተሰዶ ነበር።
እኔ ግን በትምህርቴ ኮሌጅ እስካጠናቅቅ ድረስ ብማርም ከዚያ በላይ መግፋት አልቻልኩም ነበር።
ይህም እጮኛዬ በኬንያ ውስጥ በችግር ረዥም ዓመታትን ስላሳለፈ ነበር። እሱ ጋርም መሄድ እንደነበረብኝ ውስጤ ያስገድደኝ ነበር። በዚሁ ምክንያት ሃገሬን ትቼ ወደ ኬንያ ጉዞዬን ጀመርኩኝ።
ወደ ኬንያ ሳቀና ማንኛውንም ችግር ከእጮኛዬ ጋር ሆኜ ለመጋፈጥ ዝግጁ ነበርኩኝ። ፍቅር ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም እግዚያብሔር አሳክቶልን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ተያይዘን ወደ አውስትራሊያ መጣን።
የፎቶው ባለመብት, Qananitu G Butucha
በኢትዯጵያና በአውስትራሊያ መካከል ያለውን ልዩነት በቃላት መግለጽ ያስቸግረኛል። ይህች ያደገችና ርቃ የሄደች ሃገር ናት።
በእድገቷም ሰብዓዊ መብት የሚጠበቅባት እና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሃገርም ጭምር ናት።
አውስትራሊያ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ሰዎች በመኖራቸው የበርካታ ሃገራት ምግብ ይገኛል። በዚህም ምክንያት የአውስትራሊያ ባህላዊ ምግብ የሚባል ነገር ማግኘት ከባድ ነው።
ያም ቢሆን ግን ለመዝናናትም ሆነ ምግብ ለመመገብ ወደ ውጪ ስወጣ ብዙውን ጊዜ ከምመርጣቸው ምግቦች አንዱ በርገርና ቺፕስ ነው።
የፎቶው ባለመብት, Qananitu G Butucha
ከሃገሬ ብዙውን ጊዜ የማስበው ነገር ቢኖር የሚያኮራውን ባህላችንን ነው። አብሮ የመኖር ባህል በተለይ በገጠር ያለው በፈረስ የሚደረገውን የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ሁሌ እናፍቃለሁ።
እኔም ዕድሉ ገጥሞኝ እንደ ባህላችን በፈረስ አግብቼ ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር።
በሜልበርን ከተማ ውስጥ ከምጎበኛቸውና ለመዝናናት ከምመርጣቸው ቦታዎች ዋነኛው 'ሴንት ኪልዳ ቢች' የተሰኘው በውሃ ዳርቻ ያለው ስፍራ ነው።
በተለይ ፀሐይ ከባሕሩ ጀርባ ስትጠልቅ መመልከት ያስደስተኛል። ወደ አውስትራሊያ በመምጣቴ ሰላም ባለፈ ትልቅ ነገር አግኝቼበታለሁ የምለው ነገር ቢኖር የትምህርት ዕድልና በተማርኩበት ሙያ ሰዎችን መርዳት መቻሌ ነው።
የፎቶው ባለመብት, Qananitu G Butucha
በዚህ ሃገር የጤና ሥራ መሥራት መቻል የሚያኮራና ሕዝቡን ለማገልገል የሚቻልበት መንገድ ስለሆነ ጥሩ ዕድል ነው። ስለዚህ ይህንን ዕድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።
አቅም ቢኖረኝ እዚህ ሃገር ውስጥ መቀየር የምፈልገው ነገር ቢኖር፤ በቅርቡ የጸደቀውን ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል ጋብቻ እንዲፈጸም የሚያስችለውን ህግ መሻር ነው። ይሄ ከተፈጥሮና ከእምነቴ ጋር የሚቃረን ስለሆነ መቅረት አለበት እላለሁ።
በሌላ መልኩ ደግሞ አውስትራሊያ ከሃገራችን በብዙ መልኩ ይለያል። ስለሆነም ሃገሬ እንዲህ ብትሆንልኝ እንድል የሚያደርጉኝ ነገሮች አሉ።
በተለይ የማህበራዊ አገልግሎቱ ፍጥነት እንዴት ለሕብረተሰቡ እንደሚደርስ ሃገሬም ከዚህ ብትማር ብዬ እመኛለሁ።
መጀመሪያ ወደዚህ ሃገር ስመጣ ካጋጠሙኝ ችግሮች መካከል ከባድ የነበረው ባህሉንና ቋንቋ አለመቻሌ ነበር።
እዚህ ሃገር ይሉኝታ የሚባል ነገር የለም። ሰው ራቁቱን ሊሄድ ትንሽ ነው የቀረው። ይሄ ደግሞ ከሌላ ሃገር ለመጣ ሰው በጣም አስደንጋጭ ነው። እኔም ወደዚህ ሃገር ስመጣ ያጋጠመኝ ይኸው ነው። እንደዚህ እርቃናቸውን የሚሄዱ ሰዎች ሳይ በጣም እደነግጥ ነበር።
የፎቶው ባለመብት, Qananitu G Butuchala
ቋንቋቸውን አስተካክዬ እስከምናገር ቀላል የማይባል ችግር ይገጥመኝ ነበር። ስለሆነም ለሕዝባችን ባሉበት ሁሉ የእንግሊዘኛ ቋንቋን አጥብቀው ቢማሩ በሄዱበት ስለሚጠቅማቸው ይሄን መልዕክት ላስተላለልፍ እወዳለሁ።
በቅጽበት ካለሁበት ወደ ሃገሬ የሚወስደኝ ነገር ቢኖር ወደ ተወለድኩባትና እናቴና አባቴ ወደሚገኙባት ኩዬራ፣ ሻሸመኔ ውስጥ እራሴን ባገኘው ድስታዬ ወደር የለውም።
ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረችው
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦