ፌስቡክ በመረጃ ፍሰት ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ ነው

Mark Zuckerberg Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ለውጡ ከፍተኛ መሆኑን በዘርፉ ያሉ እየገለጹ ነው

ፌስቡክ የዜና መረጃዎችን የሚሰጥበትን አካሄድ በማሻሻል ከንግድ ድርጅቶች፣ ከተቋማትና ከመገናኛ ብዙሃን ለሚመጡ መረጃዎች የሚሰጠውን ትኩረት ዝቅ ሊያደርግ ነው።

የፌስቡክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ በገጹ ላይ እንዳስነበበው በቤተሰብ እና በጓደኛሞች መካከል ውይይት ለሚፈጥሩ ይዘቶች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል።

ፌስቡክን የሚጠቀሙ ድርጅቶች የሚለቋቸው መረጃዎች ያላቸው ተደራሽነት በዚህ ምክንያት እንደሚቀንስ ፌስቡክ አስታውቋል።

ይህ ለውጥ በመጪዎቹ ሳምንታት ተግባራዊ ይደረጋል።

"የንግድ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ተቋማት የሚያወጧቸው መረጃዎች የግል መረጃዎችን በማሳነስ የግለሰቦችን የፌስቡክ ገጽ እየሞሉት ነው፤ የሚል አስተያየት ከተጠቃሚዎች ስለደረስን ነው ግለሰቦች ብዙ ትስስር እንዲኖራቸው ለመስራት የወሰነው" ሲል ዙከርበርግ ጽፏል።

ከመሰል ድርጅቶች የሚመጡ ይዘቶች እንዲተዋወቁ የሚፈለግ ከሆነም ህብረተሰቡን የሚያወያዩ ሊሆኑ ይገባል ሲል ይገልጻል።

ውይይት የሚያጭሩ የቀጥታ የፌስቡክ ስርጭቶች እንደምሳሌ ተጠቅሰዋል።

"ይህንን ለውጥ በማድረግ ሰዎች ፌስቡክ ላይ የሚቆዩበት ጊዜ እና አንዳንድ የተሳትፎ መለኪያዎች እንደሚቀንሱ እጠብቃለሁ" ብሏል።

"ሆኖም በፌስቡክ ላይ የምታሳልፉት ጊዜ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል" ሲል ዙከርበርግ አስታውቋል።

Image copyright AFP

እ.አ.አ. በ2018 ፌስቡክን "በመጠገን" ተጠቃሚዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ እና በገጹ ላይ የሚኖራቸውን ቆይታ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራ ቀደም ሲል ዙከርበርግ አስታውቆ ነበር።

ፌስቡክን ከአንዳንድ ሃገራት እንደሚጠብቅም ቃል ገብቶ ነበር።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሩሲያን ጨምሮ አንዳንድ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉትን ይዘቶች ለመቀየር ሞክረዋ።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ሆኑት ላውራ ሃዛርድ ኦዌን "በጣም ጠቃሚ ለውጥ ነው" ብለዋል።

"አታሚዎች ላይ ይበልጥ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በገጻችን ላይ የምንመለከታቸው ዜናዎች ቁጥር አነስተኛ ነው የሚሆነው" ብለዋል።

ሆኖም ፌስቡክ የትኛዎቹን መረጃዎች ቅድሚያ በመስጠት ለመልቀቅ ዝግጁ እንደሆነ ግልጽ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።