በቱኒዚያ የተቃውሞ ሰልፍ ቀጥሏል

ተቃዋሚ ሰልፈኞች የ2018 በጀት በድጋሚ እንዲጤን እና መንግሥት ሙስናን እንዲዋጋ ጠይቀዋል Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የ2018 በጀት በድጋሚ እንዲጤን እና መንግሥት ሙስናን እንዲዋጋ ጠይቀዋል

የመንግሥት ድጎማ መቋረጥ የለበትም በሚል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተጠናክሮ ሲቀጥል ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ሰልፈኞችን በትኗል።

ሮይተርስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የፖሊስ መኪኖችን በድንጋይ ሲደበድቡ እንዲሁም ጎማዎችን ሲያቃጥሉ ታይተዋል።

ግጭቱ የተከሰተው ኤድታሜን በምትባል በዋና ከተማ ውስጥ በምትገኘ ድሆች በሚኖሩባት አካባቢ ነው።

ትናንት ፕሬዝዳንት ቤጂ ሳይድ ለወጣቶች የሥራ እድልን ለመጨመር ቃል ገብተው ነበር።

በቱኒዚያ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ የአረብ ዓብዮት ተቀስቅሶ በነበረባት ወቅት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ቤን አሊን ከ23 ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ከስልጣን አስወግዷል።

በአሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ በስደት የሚኖሩት ቤን አሊ የህዝብን ንብረት ያለአግባብ በመጠቀም በሚል ክስ በሌሉበት የ32 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያው ወር ላይ በቱኒዚያ የተቀውሞ ሰልፍ ማድረግ የተለመደ ሲሆን እኤአ 2011 በቱኒዚያ የተጀመረውን የዓረብ አብዮት ይታወሰበታል።

ተቃዋሚዎች የ2018 በጀት በድጋሚ እንዲጤን እና መንግሥት ሙስናን እንዲዋጋ ጠይቀዋል።

በሰሞኑ ተቃውሞ ከ800 በላይ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ በዘረፋ እና አመጽ በመቀስቀስ ከስዋቸዋል።

ሚንስትሩ ጨምረውም፤ 97 የጸጥታ አስከባሪ ኃይል አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተቃዋሚዎች በኩል የደረሰው ጉዳት ግን አልተነገረም።

ተቃውሞውን ተከትሎ መንግስተ የኑሮ ጫና የበረታባቸውን ዜጎች እንደሚደግፍ የአገሪቱ ባለስልጣናት ገልፀዋል። የቱኒዚያ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድሃ ዜጎች የመግዛት አቅም ከፍ በሚልበትና የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው ተጠቁሟል።

ተያያዥ ርዕሶች