የትራምፕ እቅድ “የክፍለዘመኑ ጥፊ ነው”: መሃሙድ አባስ

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት የሆኑት መሃሙድ አባስ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ (መሐከል የተቀመጡት) የፍልስጤም ፕሬዝዳንት የሆኑት መሃሙድ አባስ

የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጥረትን "የክፍለ ዘመኑ ጥፊ" ሲሉ ገልፀውታል።

የፍልስጤማውያን አመራሮች በተሰበሰቡበት አፅንኦት ሰጥተው እነደተናገሩት፤ ከአሜሪካ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርጋ ከተቀበለች በኋላ ከአሜሪካ የሚመጣ ማንኛውንም የሰላም እቅድ እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም እስራኤል በ1995 የተጀመረውን የኦስሎ ስምምነት የሰላም ሂደትን ወደጎን በማለቷ ወቅሰዋታል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፍልስጤም የሰላም ድርድሩን አልቀበልም ካለች እርዳታ ለማቋረጥ ዝተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አጨቃጫቂው እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት ውሳኔ ለሰላም ድርድሩ "ከጠረጴዛው ላይ መነሳት" ሰበብ ሆኗል ሲሉም ተናግረው ነበር።

ፍልስጤማውያን በበኩላቸው ውሳኔው የሚያሳየው አሜሪካ ገለልተኛ ሆና ልትሸመግል እንደማትችል ነው ብለዋል።

የፍልስጤም አመራሮች ለትራምፕ እርምጃ መልስ ጠንከር ያለ ምላሽ ለመስጠት ለሁለት ቀናት ያህል በራማላህ ስብሰባ ተቀምጠዋል።

ባለፈው ወር የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አሜሪካ ለእየሩሳሌም በሰጠችው እውቅና ማዘኑን ከገለፀ በኋላ አባስ የትረምፕን ምክረ ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።

ቅዳሜ እለት ለፍልስጤማውያን ፓርቲ አመራሮች በራማላህ ባደረጉት ንግግር "የክፍለ ዘመኑ ድርድር የክፍለ ዘመኑ ጥፊ ሆኗል፤ በዚህም ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

"ኦስሎ ስል ነበር፤ ነገር ግን ኦስሎ የለም፤ እስራኤል ኦስሎ እንዲያበቃ አድርጋዋለች" ሲሉም አክለዋል።

ከዋሽንግተን ምንም እንኳን ዝርዝር መረጃው ይፋ ባይሆንም ለባለፉት ወራት አዲስ የሰላም እቅድ እያረቀቀች ነው።

እየሩሳሌም በአለም ላይ ከፍተኛ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነች።

እስራኤል ሙሉ እየሩሳሌም ዋና ከተማዋ እንድትሆን ትፈልጋለች። ፍልስጤማውያን በበኩላቸው ምስራቅ እየሩሳሌምን ፣ በ1967 በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ወቅት የተያዘው፣ የወደፊቷ ፍልስጤም ዋና ከተማ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ነገርግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምንም እንኳ በቀጠናው አለመረጋጋት ይከሰታል ቢባሉም እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነትን በይፋ ተቀብለዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲንም የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ ከሆነችው ቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚዛወር ተናግረዋል።