ኦሮሚያና አማራ የሚፈቱ እስረኞችን እየለዩ ነው

የተቃውሞ ሰልፈኞች
አጭር የምስል መግለጫ የተቃውሞ ሰልፈኞች

ዛሬ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ 528 እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ እንደሚለቀቁ ተናግረዋል። ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ከሚፈቱት እስረኞች መካከል 115 በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ሥር እንደሚገኙ ጠቁመዋል። የተቀሩት 413 ደግሞ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ክልል ስም ዝርዝር አቅርቦ ክሳቸውን እንዲቋረጥ ተወስኗል ብለዋል።

ከደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ክልል በተጨማሪ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል በጉዳዩ ላይ ምን እየሰራ ነው ስንል ጠይቀናል።

የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ኮሚኒኬሽን ሃለፊ አቶ ታዬ ደንደዓ ክልሉ ''የክስ መዝገቦችን እያጣራን ነው። እሰከ ጥር 12 ድረስ አጣርተን እንጨርሳለን'' ብለዋል።

''የፖለቲካ ተሳትፎ የሚባል ወንጀል የለም። ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር ተያይዞ የታሰሩ በሙሉ ይፈታሉ።''

እንደ አቶ ታዬ ከሆነ ክልሉ እስረኞች የሚፈቱበት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ የለም። ''በሽብር፣ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመናድ ሙከራ አድርገዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸውም ይፈታሉ'' ይላሉ አቶ ታዬ።

ይሁን እንጂ በግል ጸብ የሰው ህይወት ያጠፉ ወይም አካል ጉዳት ያደረሱ ግን ይህ ምህረት አይመለከታቸውም ብለዋል።

አቶ ማሩ ቸኮል የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ክልሉ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ ነው ብለዋል። ክልሉ ልክ የፌደራል አቃቤ ሕጉ እንዳስቀመጣቸው ያሉ መስፈርቶች የሚኖሩት ሲሆን "እኛም የምንከተለው አካሄድ ተመሳሳይ ይሆናል" ብለዋል።

"ክሶችን የፌደራል ወይም የክልሉ ስልጣን የሆነውን የመለየት ስራም ይሰራል። ከዛ በኋላ የሚለቀቁትን እስረኞች ለሕዝቡም ለመገናኛ ብዙሃንም ይፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

በክልሉ የተዋቀረው ኮሚቴ ከርእሰ መስተዳድሩ፣ ከክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ እና ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ተወያይቷል ያሉት አቶ ማሩ በዚህ መግለጫ ወቅት የሚፈቱ ታራሚዎች ስም ዝርዝር ለምን አልደረሰም ለሚለው ጥያቄ የደቡብ ክልል ቀድሞ ተዘጋጅቶ ካልሆነ በስተቀር ታራሚው በርካታ ስለሆነ እና የማያዳግም ስራ ለመስራት እንዲያስችል እየሰራን ነው።

"ከዚህ በላይ ባይዘገይ እኔም ደስ ይለኛል ታራሚዎቹ ተለይተው እንዳለቁም ይፋ እናደርጋለን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ