በካሊፎርኒያ 13 ልጆች በቤታቸው ውስጥ በሰንሰለት ታስረው ተገኙ

የ57 ዓመቱ ዴቪድ ተርፒን እና የ49 ዓመቷ ባለቤቱ ሉዊዝ አን Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ሁለቱ ወላጆች፤ ልጆችን በማሰቀየት እና አደጋ ላይ መጣል የሚሉ ክሶች ተመስርቶባቸዋል።

ሁለት ወላጆችን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ 13 ልጆቻቸውን በሰንሰለት አስረው በማቆየታቸው በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የካሊፎርኒያ ፖሊስ አስታወቀ።

የ57 ዓመቱ ዴቪድ ተርፒን እና የ49 ዓመቷ ባለቤቱ ሉዊዝ አን ልጆችን በማሰቀየት እና አደጋ ላይ መጣል የሚሉ ክሶች ተመስርቶባቸዋል።

ካሊፎርኒያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በሰንሰለት ታስረውና ተቆልፎባቸው የተገኙት ልጆች እድሜያቸው ከ 2-29 እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ጨምሮ እንዳስታወቅም ታስረው የተገኙት 13ቱ ሰዎች ወንድምና እህት ናቸው።

የፖሊስ አዛዡ በሰጡት መግለጫ፤ ፖሊስ ከቦታው መድረስ የቻለው ከታሳሪዎቹ መካከል የ10 ዓመት እድሜ ያላት ህጻን አምልጣ ቤቱ ውስጥ ባገኘችው ተንቀሳቃሽ ስልክ ወደ ፖሊስ ከደወለች በኋላ ነው ብለዋል።

የ10 ዓመቷ ህጻን ወደ ፖሊስ ደውላ ሌሎች 12 ወንድም እና እህቶቿ በወላጆቻቸው ታስረው እንደሚገኙ ተናግራለች።

ፖሊስ በቦታው ሲደርስ በምግብ እጥረት የተጎሳቆሉ እና ንጸህና በጎደለው ጨለማ ክፍል ውስጥ የታሰሩ 12 ሰዎችን ማግኘቱን ተናግሯል።

ወላጆቹ ልጆቻቸውን ለምን በዚህ አይነት ሁኔታ እንዳቆዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ መስጠት አልቻሉም።

ፖሊስ ከታሳሪዎቹ መካከል 7ቱ እድሜያቸው ከ18-29 የሚገመቱ አዋቂ መሆናቸው ድንጋጤን ፈጥሮብኛል ብሏል።

13ቱም ልጆች አሁን በአካባቢው በሚገኙ ሆስፒታሎች እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።