''በቂ መጠለያ ባለመገኘታችን ዛፍ ሥር እያደርን ነው''

ተፈናቃዮች
አጭር የምስል መግለጫ የባሌ ዞን ተፈናቃዮች ለዘርፈ ብዙ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ።

በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ከሶማሌ ክልል በመሸሽ ባሌ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች የውሃ እና የምግብ እጥረት አጋጥሞናል በአጠቃላይ በቂ ትኩረት አልተሰጠንም ሲሉ እያማረሩ ነው።

ከአምስት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሸሽተው በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ጉራ ዳሞሌ በሚባል ወረዳ ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙ ዜጎች አንዱ የሆኑት ሼህ አህመድ ኢያ መንግሥት እና ህዝቡ ድጋፍ ቢያደርግልንም አሁንም በርካት ችግሮች አሉብን ይላሉ።

በሌሎች መጠለያ ካምፕ እንደሚታየው በቂ የሆነ መጠለያ እንደሌላቸው የሚናገሩት ሼህ አህመድ፤ በሰጠን የሸራ መጠለያ ውስጥ ነው እየኖርን የምንገኘው ይላሉ።

''ዋነኛው ችግራችን መጠለያ ነው። አሁን ዛፍ ሥር ነው እያደርን ያለነው። ቅያር ልብስም የለንም። ቀይ መስቀል ብርድ ልብስ ቢሰጡንም በቂ አይደለም'' ሲሉ ይናገራሉ።

ከ16 ሺ በላይ ተፈናቀዮች የሰፈሩባት ወራዳ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዳሉባት የወረዳዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ለ19 ዓመታት ከኖሩበት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ግጭት በመሸት ቤት እና ንብረታቸውን ጥለው ወደ ጉራ ዳሞሌ ወረዳ እንደመጡ የሚናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ፋይዳ ናቸው።

ወይዘሮ ፋይዳ ''የ10 ወር ጨቅላ፣ የሦስት እና የስድስት ዓመት ልጆቼን ይዤ ነው ወደእዚህ የመጣሁት። በዚህ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ መኖር ስለማይቻል ወደ ከተማ ሄጄ በሰው ቤት ተቀጥሬ ልጆቼን ለማሳደግ ጥረት ላይ ነኝ'' ሲሉ ይናገራሉ።

''በምግብ እጥረት የተራበ የለም''

የባሌ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አብረሃም ኃይሉ በበኩላቸው ተፈናቅለው ለመጡ ዜጎች መንግሥት እና ህዝቡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉላቸው ነው ይላሉ።

አቶ አብረሃም ''ተፈናቃዮቹ በረሃማ ስፍራ ላይ ተጠልለው ስለሚገኙ የውሃ እጥረት አጋጥሟል፤ ለዚህም ተጨማሪ የውሃ ማመላለሻ መኪናዎች እንዲሰጡን ለሚመለከተው የክልሉ ቢሮ ጥያቄ አቅረበን እየተጠባበቅን ነው'' ይላሉ።

ይሁን እንጂ ''በምግብ እጥረት የተራበ የለም'' ሲሉ አቶ አብረሃም ይናገራሉ።

''የእርዳታ ሥራውን ለማስተባበር ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን ወረዳዎች ተመልክቻለሁ፤ እስካሁን ድረስም በምግብ እጥረት ምክንያት የተራበ ወይም ህይወቱ አደጋ ላይ የወደቀ ዜጋ የለም። እንደውም ተፈናቃዮች የሚደረግልን ድጋፍ ይቀጥል የሚል በጎ አስተያየት ነው የሚሰጡን'' ይላሉ።

የተፈናቃዮች ድጋፍ አስተባባሪና መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ዶክተር አበራ ዴሬሳ ''እኔ እስከማውቀው ድረስ ለተፈናቃዮች የምግብ እና ቁሶች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው'' ይላሉ።

''የእርዳታ ምግብ በየሁለት ሳምንቱ እየተጓጓዘ ነው። የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ እና ተበታትነው ስለሰፈሩ እርዳታውን በሚፈለገው መጠን እና ፍጥነት ማድረስ ላይ ችግር አለ'' ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።

አጠቃላይ ሁኔታ

ከባሌ ዞን የአደጋ መከላለክለ እና ዝግጁነት ቢሮ የተገኘው አሃዝ እንደሚያሳየው በዞኑ በሚገኙ 8 ወረዳዎች ውስጥ 111 ሺህ በላይ ተፈናቀዮች ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከል 64 ሺ የሚሆኑት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበረ ላይ ይኖሩ የነበሩ ነገር ግን ግጭቱን በመሸሽ የመጡ ናቸው።

ተያያዥ ርዕሶች