የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በበጀት ጉዳይ አልተስማሙም

ካፒቶል ሂል Image copyright EPA

እንደ አውሮፓውያኑ የ2018 የአገሪቱን በጀት በሚመለከት የአሜሪካ ሴኔት አባላት ስምምነት ላይ መድረስ ተስኗቸዋል። በአገሪቱ ሁሌም የበጀት ዓመት የሚጀምረው ጥቅምት አንድ ላይ ቢሆንም ሴኔቱ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ይህ ቀነ ገደብ ተጥሷል።

የመንግሥት ተቋማትም በጊዜያዊነት ካለፈው ዓመት በተራዘመ በጀት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

አሁን ግን ቀነ ገደቡን መጠበቅ ባለመቻሉ የመንግሥት ተቋማት ከተዘጉ ሁለት ቀናት ተቆጥረዋል። ለዚህ ደግሞ ሪፐብሊካንና ዲሞክራቶች እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ነው።

ትናንት በተደረገው የሴኔቱ ስብሰባ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ንግግሩ እንደገና ወደ ሰኞ እኩለ ቀን ተላልፏል።

ዲሞክራቶች ስምምነት ላይ መደረስ ካለበት ትራምፕ የስደት ጉዳይን በበጀቱ ውስጥ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ፤ ሪፐብሊካን ደግሞ የመንግሥት ተቋማት ዝግ ሆነው እያለ ምንም አይነት ስምምነት ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

ትራምፕ የሴኔቱ አለመግባባት በአብላጫ ድምፅ እንዲፈታ ጥሪ አስተላልፈዋል። በሴኔቱ ደንብ በጀቱን የሚመለከተው አዋጅ ለመፅደቅ 60 ድምፅ ሊያገኝ ይገባል።

ይህ ማለት ደግሞ ከሴኔቱ መቶ መቀመጫ 51ዱን የያዙት ሪፐብሊካን ይህ አዋጅ እንዲፀድቅ የተወሰኑ ዲሞክራቶች ድምፅ ያስፈልጋቸዋል።

ትራምፕ ግን አብላጫ ድምፅ አለመግባባቱን ይቋጨዋል እያሉ ነው። እሳቸው የሰነዘሩት ይህ መፍትሄ ግን ብዙም ግልፅ አይደለም ተብሏል።

አንድ ፓርቲ ማለትም ሪፐብሊካኖች ኮንግረሱንም ዋይት ሃውስንም ተቆጣጥረው እያለ የመንግሥት ተቋማት በበጀት አለመፅደቅ ሲዘጉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አርብ እለት የተካሄደው ድምፅ አሰጣጥ 50 ለ49 ነበር።

ዲሞክራቶች በልጅነታቸው ወደ አሜሪካ የገቡ 700 ሺህ ስደተኞች ከአሜሪካ እንዳይባረሩ ከለላ እንዲሰጣቸው፤ ለዚህም በጀት እንዲመደብ ይፈልጋሉ።

በበጀት ስምምነት ላይ የሚያስቀምጡት ዋና ቅድመ ሁኔታም ይህው ነው። በተቃራኒው ሪፐብሊካኖች ደግሞ ድንበርን በግምብ ማጠርን ጨምሮ ለድንበር ደህንነት በጀት እንዲመደብ፣ የአገሪቱ የስደተኞች ፖሊሲ ላይም ማሻሻያ እንዲደረግ ይፈልጋሉ። ለጦር ኃይልም የሚበጀተውም እንዲጨምር ይሻሉ።