ትራምፕን ለመቃወም ብቻውን አደባባይ የሚወጣው ኢትዮጵያዊ

ኢትዮጵያዊው ወጣት ትራምፕን ሲቃወም Image copyright Tsegaye Hailesilassie
አጭር የምስል መግለጫ 'ትራምፕ ቆሻሻው አንተ ነህ'

ፀጋዬ ኃይለስላሴ ነዋሪነቱን የደረገው በአሜሪካዋ የሜኒሶታ ግዛት ውስጥ ሴንት ፖል በምትባል ከተማ ውስጥ ሲሆን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ለብቻው ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ዶናልድ ትራምፕን እየተቃወመ ይገኛል።

''ትራምፕን ስቃወም ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም'' የሚለው ፀጋዬ፤ በተለያየ ወቅት ትራምፕን የሚቃወሙ የተለያዩ ጽሁፎችን እንዲሁም የራሱን የቪዲዮ ምስሎች በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደሚለጥፍ ይናገራል።

ትራምፕ የአፍሪካ፣ ሄይቲን እና ኤልሳልቫዶር ሃገራትን እና ስደተኞችን በተመለከተ የተናገሩት አጸያፊ ንግግር ቅዋሜዬን አደባባይ ይዤ እንድወጣ አስገድዶኛል በማለት ፀጋዬ ይናገራል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ትራምፕን ለመቃወም ብቻውን አደባባይ የሚወጣው ኢትዮጵያዊ

''ትራምፕ የተናገረውን ስሰማ በጣም ነበር የተበሳጨሁት። ውስጤ እርር ነበር ያለው። በጣምም አዝኜ ነበር። ውስጤ የተፈጠረው ንዴት፣ ቁጭት እና እልህ ሥራዬን አቋርጬ ለተቀውሞ እንድወጣ አደረገኝ'' ሲል ይናገራል።

''ቀድሞውንም ለስደተኞች ያላቸው አመለካከት ያበሳጭኝ ነበር'' የሚለው ፀጋዬ የትራምፕ ባለቤት ስደተኛ መሆኗ እንዲሁም ትራምፕ በአንድ ወቅት በአደባባይ 'የጀርመን ደም ስላለብኝ ኩራት ይሰማኛል' ማለታቸውን ያስታውሳል።

ትራምፕ ''ቆሻሻው አንተ ነህ''

ፀጋዬ ትራምፕን ለመቃወም 'trump you'RE THE SHITHOLE' ወይም 'ትራምፕ ቆሻሻው አንተ ነህ' የሚል መፈክር ይዞ አደባባይ ወጥቷል። ፀጋዬ እንደሚለው የመፈክር አጻጻፉ የራሱ የሆነ ትርጓሜ አለው ይላል።

ፀጋዬ ሲያስረዳ ''በመፈክሩ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቃላት 'trump' እና 'you' በእግሊዝኛ ትንሽ በሚባሉት ፊደላት (ስሞል ሌተርስ) ነው የጻፍኳቸው ይላል። ይህም የሰውዬው አስተሳሰብ የወረደ መሆኑን ይገልጻል። ቃላቱን በቢጫ ቀለም የጻፍኳቸው ደግሞ ትራምፕን እንዲመስሉ ነው'' ይላል።

'THE SHITHOLE' የሚሉት ሁለት ቃላት ደግሞ እኔ ለትራምፕ የሰጠሁት ቅጽል ስም ነው በማለትወ ፀጋዬ ያስረዳል።

Image copyright Tsegaye Hailesillasie

በዚህ መልኩ መፈክሩን ካዘጋጀ በኋላ ሰዎች በብዛት በሚገኙበት ሴንት ፖል ከተማ በመዘዋወር እና መኪናው ላይ በመስቀል ተቃውሞውን ያሰማል።

''ከመኪናዬ ዘፈኖችን በመክፈት በውዝዋዜ እና በሽለላ ጭምር የታጀበ ተቀውሞ ስለማሰማ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ እየቻልኩ ነው'' ሲል ፀጋዬ ይናገራል።

የአንድ ዓመት አፈና

ፀጋዬ በሚኖርበት የአሜሪካ ግዛት ውስጥ የዲሞክራት ፓርቲ ደጋፊዎች በብዛት ስለሚገኙ ለፀጋዬ ድጋፋቸውን ይገልፃሉ።

ይሁን እንጂ ትራምፕን በመቃወሙ ድጋፋቸውን የሰጡት እንዳሉ ሁሉ በሥራው ደስተኛ የልሆኑም በርካቶች ናቸው።

የዘር ጥላቻ የሚያራምዱ እና የትራምፕ ደጋፊ የሆኑ ሰዎች በማደርገው ድርጊት ይበሳጫሉ ይላል ፀጋዬ።

''አንድ ቀን አንድ ሰውዬ በመኪናው ሊገጨኝ ሞክሮ ነበር። በጣም ተጠግቶች ጸያፍ ስድብ ተሳድቦ ሄደ'' ሲል የጋጠመውን ይናገራል።

ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ አቅራቢያ ወደ ሚገኝ አየር ማረፊያ ሄዶ ተቃውሞውን ሲያሰማ፤ ፖሊሶች አስገድደው ከአየር ማረፊያው ክልል እንዳስወጡት እና ወደ ኤርፖርቱ ድርሽ እንዳይል የአንድ ዓመት እገዳ እንደተጣለበትም ተናግሯል።

አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም

''ከእኔ ጎን በመቆም ትራምፕን የሚቃወሙ እና የእኔን ተግባር የሚደግፉ ነጮች እንዳሉ ሆነው፤ ኢትዮጵያዊያን እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጎችን ለተቀውሞ ሰልፍ ብጠራም ማንም አልተገኘም'' በማለት ፀጋዬ ይናገራል።

ግሪን ካርድ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ስለሌለኝ ከዚህ ተግባሬ እንድቆጠብ ብዙዎች ያስጠነቅቁኛል የሚለው ፀጋዬ፤ ተቃውሞውን ከማቋረጥ ይልቅ አሁንም ሌሎች ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪውን ያስተላልፋል።