ሙጋቤ ቅንጡ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ ተባለ

ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ Image copyright Reuters

የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ሙጋቤና ቤተሰባቸው በሰላም እንዲኖሩ መተው እንዳለባቸው ተናገሩ።

በቅንጡ ህይወታቸውና በተጋነነ ወጪ የሚታወቁት ሙጋቤና ቤተሰባቸው በመጨረሻ ተጠያቂ ይሆናሉ ብሎ ህዝቡ ቢጠብቅም፤ ምናንጋግዋ ሙጋቤ ከነጥቅማጥቅማቸው ከቤተሰባቸው ጋር በሰላም ይኑሩ ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ምናንጋግዋ ማንም ተጠያቂ የሆነ ሰው ከክስ ነፃ እንደማይሆን ይናገራሉ።

የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት በመባል ትታወቅ የነበረችው ዚምባብዌ ህዝቧን ለመመገብ ስትታገል የሙጋቤ ባለቤት በራሳቸው ላይ ገንዘብ ይረጩ ነበር ይባላል።

ግሬስ ውድ ቁሳቁሶችን ከመውደዳቸው የተነሳ ከትልልቅ ዓለም አቀፍ ብራንዶች አንዱ በሆነው ጉቺ 'ጉቺ ግሬስ' ተብለውም ይጠሩ ነበር።

ምናንጋግዋን ጨምሮ ሙጋቤና ባለስልጣናቶቻቸው በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ፣ በድብደባና አስገድዶ በመድፈር ጭምር ይወነጀሉ ነበር።

ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉት ምናንጋግዋ ደግሞ አገሪቱን ከሙስና አፀዳለው ብለዋል።

ለማንም ከመከሰስ ነፃ የመሆን መብት አለመስጠታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ምናንጋግዋ "አዲሱ የዚምባብዌ አስተዳደር ሙጋቤና ቤተሰባቸው በሰላም እንዲኖሩ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል"ብለዋል ።

ምናንጋግዋ እንዳሉት ሙጋቤ የመኪና፣ የፀሃፊዎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ በረራ፣ የሴንጋፖር ጉብኝትና የህክምና የመሰሉ ጥቅማጥቅሞቻቸውን ማግኘት ይቀጥላሉ።

ይህ ደግሞ ሙጋቤና ቤተሰባቸው ቅንጡ ኑሮ መምራትን ይቀጥላሉ ማለት ነው። ምናንጋግዋ ስለ ጥቅማጥቅሙ የገንዘብ ስሌት ያሉት ነገር ባይኖርም ብዙዎች አጠቃላይ ወጪው አስር ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ እየገለፁ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች