ኩባ፡ የፊደል ካስትሮ ልጅ 'ራሱን አጠፋ'

Fidel Castro Diaz-Balart at an event in Image copyright AFP/Getty
አጭር የምስል መግለጫ ከአባቱ ጋር በነበረው መልክ መመሳሰል ምክንያት 'ፊደሊቶ' በሚል ቅጽል ስም በስፋት ይታወቅ ነበር

የ68 ዓመቱ የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ ልጅ ራሱን ማጥፋቱን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ።

ፊደል ኤንጅል ካስትሮ ዲያዝ-ባላርት ሐሙስ ጠዋት ሞቶ የተገኘ ሲሆን በድብርት ሲሰቃይ ነበር ተብሏል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልጅ ከአባቱ ጋር በነበረው የመልክ መመሳሰል "ፊድሊቶ" ወይንም ትንሹ ፊደል የሚል ቅጽል ስም ነበረው።

በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በኒውክለር ፊዚስከስ የሰለጠነ ባለሙያ ነበር።

"በከባድ ድብርት ምክንያት ለወራት በዶክተሮች የህክምና ክትትል ሲደረግለት የነበረው ፊደል ካስትሮ ዲያዝ-ባላርት ዛሬ ጠዋት ሕይወቱን አጥፍቷል" ሲል የኩባው ግራንማ ጋዜጣ አስነብቧል።

ከሆስፒታል ቆይታ በኋላ ባለፉት ወራት ከቤቱ ሆኖ ህክምና ሲከታተል እንደነበር የሃገሪቱ ቴሌቪዥን አስታውቋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ብዙ መጽሐፎችን የጻፈው ፊደል ኤንጅል ካስትሮ ዲያዝ-ባላርት ሃገሩን ወክሎ ወደ ተለያዩ ሃገራት ተጉዟል

ህይወቱ ባለፈበት ወቅት የኩባ መንግሥት ካውንስል አማካሪ እና የኩባ ሳይንስ አካዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር።

እ.አ.አ ከ1980 እስከ 1992 ድረስ የደሴቷ ሃገርን ኒውክለር ፕሮግራም የመራ ሲሆን ፕሮግራሙ ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ካስትሮ ዲያዝ-ባላርት ከአባቱ የመጀመሪያ ሚስት ሚርታ ዲያዝ-ባላርት ነው የተወለደው።

የተወሰኑት የእናቱ ቤተሰቦች በፍሎሪዳ በሚገኘው እና ካስትሮን በመቃወም በሚታወቀው ማህበረሰብ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ያላቸው ሲሆን ማሪዮ ዲያዝ-ባላርት የተባለው ቤተሰቡ ደግሞ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ነው።

የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በቤተሰቡ በኩል እንደሚዘጋጅ የገለጸው ቴሌቭዥን ጣቢያው ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥቧል።

የአብዮት ምልክት እና ረዥም ጊዜ በስልጣን ከቆዩ የዓለም መሪዎች መካከል የሆኑት አባቱ ፊደል ካስትሮ እ.አ.አ በ2016 ነበር በዘጠና ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈው።