ኤ ኤን ሲ ጃኮብ ዙማን ከሥልጣን ሊያወርድ ነው

South African President Jacob Zuma in the capital, Pretoria, August 19, 2017. Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ዙማ ከስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደሉም ተብሏል

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣን እንዲለቁ ግፊት በበዛባቸው በአሁኑ ወቅት የሃገሪቱ ገዢ ፓርቲ ከፍተኛ አባላቱን ለመጪው ረቡዕ ስብሰባ ጠርቷል።

ኤ ኤን ሲ በመግለጫው እንዳስታወቀው ሰብሰባው የተጠራው "በሽግግር አስተዳደር" ላይ ለመወያየት ነው።

ሰኞ ዕለት ከፍተኛ ፖለቲከኞች በዙማ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ በጆሃንስበርግ አካሂደዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሙስና መወንጀላቸውን ተከትሎ ከስልጣን እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

ጃኮብ ዙማ መንበራቸውን ከለቀቁ ባለፈው ታህሳስ የኤ ኤን ሲ መሪ በመሆን የተመረጡት ሲይሪል ራማፎሳ በምትካቸው ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሰኞ በነበረው ስብሰባ ፕሬዝዳንት ዙማን ከስልጣን ማውረድ አጀንዳ እንዳልነበር የፓርቲው ቃል አቀባይ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ ስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝዳንት ዙማ በመጪው ሐሙስ መግለጫ የሚሰጡ ሲሆን አንዳንዶች ከዚህ መግለጫ በፊት ከስልጣን እንዲለቁ ይፈልጋሉ።

ነገ ደግሞ የፓርቲው ብሄራዊ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይሰበሰባል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ዙማ እንዲጠሩ ከወሰነ ፕሬዝዳንቱ አሻፈረኝ ለማለት ይቸግራቸዋል ተብሏል።

ካልሆነም በፓርላማው የመተማመኛ ድምጽ ሊሰጥባቸው ይችላል።

በአፓርታይድ ትግል ወቅት ታጋይ የነበሩት እና በአንድ ወቅት ታስረው የነበሩት ፕሬዝዳንት ዙማ እሁድ ከኤ ኤን ሲ ስድስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ቢወያዩም ከስልጣን እንዲወርዱ የቀረበላቸውን ሃሳብ አልተቀበሉትም።

የቀድሞው የኤ ኤን ሲ አባልና የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ጁሊየስ ማሌማ በትዊተር ገጻቸው ዙማ ከስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ብለዋል።

ያልተረጋገጡ ምንጮች ደግሞ ዙማ በእሑዱ ስብሰባ እሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ያለመከሰስ መብት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ብለዋል።


ምን ዓይነት ክሶች በዙማ ላይ ቀረቡ?

  • 2005: በ1999 በተካሄደ የጦር መሳሪያ ግዢ ወቅት ሙስና ፈፅመዋል ተብለው ተከሰሱ። ሆኖም ክሱ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው ከጥቂት ጊዜያት በፊት ውድቅ ተደረገ።
  • 2016: በግዢው ምክንያት በ18 የሙስና ክሶች እንዲጠየቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስተላለፈ
  • 2005: በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ቢከሰሱም በ2006 ነጻ ተብለዋል
  • 2016: የገቡትን ቃለ መሃላ በመጣስ በመንግስት ገንዘብ ንካንድላ የሚገኘውን መኖሪያ ቤታቸውን አድሰዋል ብሎ ፍርድ ቤት ሲወስንባቸው ገንዘቡን ከፈሉ።
  • 2017: ሀብታም ከሆኑት ከጉፕታ ቤተሰቦች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው ያገኙት ጥቅም አለ በሚል የሃገሪቱ አቃቤ ህግ ማጣሪያ እንደሚያካሄድ አስታወቀ። ፕሬዝዳንቱም ሆኑ የጉፕታ ቤተሰብ አባላት ክሱን አስተባበሉ።
  • 2018: ዙማ ማጣሪያው እንዲካሄድ ፈቀዱ።

ተያያዥ ርዕሶች