ኤ ኤን ሲ -ጃኮብ ዙማ ከስልጣን መውረድ አለባቸው

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, AFP / Getty Images

ፕሬዝዳንት ዙማ ከስልጣን ለመውረድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ ኤ ኤን ሲ በህጉ መሰረት ከስልጣን እንዲወርዱ እንደሚጠይቅ የሚዲያ ዘገባዎች ያስረዳሉ።

ገዢው ፓርቲ በይፋ እቅዱን ያላሳወቀ ሲሆን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን እና ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ከ ዙማ ጋር ረዥም ሰአት የፈጀ ንግግር ቢያደርጉም መቋጫ ላይ ባለመድረሳቸው ነው ወደዚህ ውሳኔ የመጡት።

የ 75 አመቱ ዙማ ሀሳባቸውን ካልቀየሩ የሕዝብ እንደራሴው የመተመመኛ ድምፅ እንዲሰጣቸው መጠየቁ አይቀርም፤ ያ ደግሞ የመሆን እድሉ አናሳ ነው።

ከ 2009 ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩት ዙማ በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው በተደጋጋሚ ይወነጀላሉ።

ራማፎሳ የፓርቲ ሊቀመንበርነት ስልጣኑን ከያዙ ጀምሮ ዙማ ከፕሬዝዳንትነት ይውረዱ የሚለው ግፊት ቢያይልባቸውም እርሳቸው ግን በእንቢተኝነታቸው ፀንተዋል።

ዙማ ዛሬ በስርአቱ መሰረት ለሚቀርብላቸው ከስልጣን ይልቀቁ ጥያቄ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ አይታወቅም።

ደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ ኤ ኤን ሲ የፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን የወደፊት ዕጣፈንታ ለመወሰን በቅርቡ ስብሰባ የሚያደርጉ ሲሆን ከስልጣን አንዲወርዱ እንደሚጠይቋቸውም እየተነገረ ነው።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሲሪል ራማፎሳ "ይህ ጉዳይ በፍጥነት እንዲቋጭ እንደምትፈልጉ እናውቃለን" ሲሉ የኔልሰን ማንዴላን 100ኛ የልደት በአል ለማክበር ለተሰበሰበው ሕዝብ መናገራቸው ይታወሳል።

ከዚህ በፊት ከፕሬዝዳንቱ ጋር "ውጤታማ እና ገንቢ ውይይት" ማድረጉን ፓርቲው አስታውቆ ነበር።

የቀረቡባቸውን የሙስና ውንጀላዎች ተከትሎ የኤ ኤን ሲ አባላት ዙማ ከስልጣን እንዲለቁ ግፊት በማሳደር ላይ ናቸው።

የሃገሪቱ ፓርላማ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሊደረግ የነበረውን ብሔራዊ መግለጫ ባልተለመደ መልኩ ወደ ሌላ ቀን እንዲተላለፍ ወስኗል።

የደቡብ አፍሪካው ታይምስ ላይቭ ድረ-ገጽ ስማቸው ያልተገለጹ ሰዎችን ጠቅሶ ትክክለኛ ድርድር ከተካሄደ ዙማ ስልጣን ለመልቀቅ ተዘጋጅተዋል ብሏል።

ከፍተኛው የአመራር ቡድን ያለ ፕሬዝዳንቱ ስምምነትም ቢሆን ከስልጣናቸው ሊያነሳቸው ይችላል።

የ75 ዓመቱ ዙማ ባለፈው ታህሳስ ነው ከፓርቲ መሪነታቸው ተነስተው ምክትላቸው በነበሩት ራማፎሳ የተተኩት።

ባለፈው ሳምንት የኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲለቁ ምክሩን አስቀምጧል።

የኤ ኤን ሲ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሚያደርገው ስብሰባው በፕሬዝዳንቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ይወስናል።

ፓርቲው ድጋፉን ሙሉ ለሙሉ የሚነፍጋቸው ከሆነ ዙማ በፓርላማው ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ስለማይኖራቸው ከስልጣን ለመልቀቅ ይገደዳሉ።

ባለፈው እሁድ የፓርቲው ስብሰባ በጆሃንስበርግ የተካሄደ ሲሆን፤ የስብሰባው ተሳታፊዎች እንዳስታወቁት ከሆነ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በአብዛኛው ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ስልጣን ላይ በሚገኙት ፕሬዝዳንት የሚደረገው ብሔራዊ መግለጫ በደቡብ አፍሪካ በዓመቱ ውስጥ ከሚደረጉ ዋነኛ የፖለቲካ ጉዳዮች አንደኛው ነው።

እንደ ብሄራዊ ጉባኤው ቃል አቀባይ ባሌካ ምቤቴ ከሆነ ፓርላማው ብሔራዊ መግለጫው እንዲቀር የወሰነው "ረብሻ እንዲፈጠር ጥሪ ሊቀርብ ይችላል" በሚል ስጋት ነው።

"ፕሬዝዳንቱ ጊዜው እንዲራዘም የጠየቁት በአንዳንድ ጉዳዮች ለውጥ ነው" ሲል የዙማ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።