ኦሮምኛ የፌዴራል ስራ ቋንቋ የመሆን ጥያቄ

Afaan Oromoo

ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን እንደሚሰራ ኦህዴድ የሰሞኑን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲጠናቀቅ ከደረሰባቸው ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ይህንንም መግለጫ ተከትሎ በብዙዎች ዘንድ መወያያም ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ጥላሁን የኦሮምኛ የፌዴራል ስራ ቋንቋ የመሆን ውሳኔን የሚደግፉ ሲሆን በአዲስ አበባ የሚኖር ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎቶችን በራሱ ቋንቋ እንዲያገኝ እንደሚረዳ

ይናገራሉ።

የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶክተር ብርኃነ መስቀል አበበ ሰኚ በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ የሚያነሳቸው ከሚያነሳቸው ሶስት ጥያቄዎች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች በተጨማሪ ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ማድረግ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ይገልፃሉ።

"የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሹ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነው። ስለዚህ የአገሪቱን እድገት ለማፋጠንና እንዲሁም ሰላሟንም ለማረጋገጥ ይህ ውሳኔ ትልቅ ድርሻ አለው። " ይላሉ።

የኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስማምተው እንዲኖሩም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ዶክተር ብርኃነ መስቀል ያስረዳሉ።

የህግ ባለሙያና በፌዴራሊዝም ብዙ ጥናቶችን ያካሄደው ውብሸት ሙላት በበኩሉ ኦሮምኛን ተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ማድረግ የበለጠ ኃገራዊ መግባባትና አንድነትን እንደሚያዳብር ይገልፃል።

"የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ኦሮምኛን ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ሲጠይቅ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ለዚህ ምላሽ መስጠት የህዝብን ጥያቄ መመለስ ብሎም ህዝቡ መንግሥት ላይ የሚኖረውን አመኔታ ወይም አቀባበልም ይጨምራል" ይላል።

በተጨማሪም "ኦሮሞን የሚያክል የህዝብ ቁጥር እያለ የስራ ቋንቋ አለማድረግ በራሱ ፍትሃዊ አይሆንም።" ይላል

በርካታ ኃገራት ከአንድ በላይ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዳላቸው የሚገልፀው ውብሸት እንደምሳሌነትም ደቡብ አፍሪካ 11 የስራ ቋንቋ እንዲሁም ቦሊቪያ 36 የስራ ቋንቋ እንዳላቸውም ይገልፃል።

"እኛም ሀገር የሀረሪ ክልልን ብንወስድ የስራ ቋንቋው ሁለት ነው እነሱም የሀረሪ ቋንቋና ኦሮምኛ ናቸው" ይላል

እስከዛሬ ድረስ ዘግይቷል የሚለው አቶ ውብሸት "የአንዳንድ ሰዎችም ፍራቻ ኦሮምኛን ተጨማሪ ቋንቋ ማድረግ አማርኛ ላይ ሌላ የሚያስከትለው ነገር የሚመስላቸው አሉ ግን ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ማድረጉ አማርኛ ላይ ምንም የሚያመጣው ተጽእኖ አይኖርም ፤ አማርኛ ቋንቋ እንዲጠፋ ሊያደርግ የሚችልበት ነገር የለም" ይላል።

ስራ ላይ ማዋል

ኦሮምኛን የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ለመተግበር ሁለት ትልልቅ ስራዎች በቅድመ-ሁኔታ መሰራት እንዳለባቸው ዶክተር ብርኃነ መስቀል ይገልፃሉ።"

"የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌው) የአፋን ኦሮሞ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን የሚሰራ ኮሚቴ አዋቅሮ መስራት ይጠበቅበታል" ይላሉ

በሁለተኛ ደረጃ የሚያነሱት ደግሞ

"የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ በተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን መስራት አለባቸው" ይላሉ

ቋንቋው እስከሚዘጋጅ ቢያንስ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ሊወስድ ስለሚችል የሚናረው ውብሸት በበኩሉ "የተለያዪ ሰነዶችን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ መተርጎም እንደገና አስተርጓሚ መቅጠር በተጨማሪ ቋንቋ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ማስተማርም ቋንቋውንም እንዲችሉ ማድረግ" እንደ ቅድመ ሁኔታም የሚያስቀምጣቸው ናቸው።