የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፈተና እና ተስፋ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች

መንግስት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የተጠመደ ሲሆን ይህም የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ መናኸሪያ ለመሆን የሚደረገውን ጥረት ማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን በመቅረፍም ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ሲል ይሟገታል።

አንዳንድ ባለሞያዎች ግን ውጥኑ እንደብዙ ዕቅዶቹ ሁሉ የተለጠጠ ነው ሲሉ ይተቹታል።

በሌላ በኩል በፓርኮቹ በሚገኙ ፋብሪካዎች የሠራተኞች ደመወዝ አነስተኛ ከመሆን ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ፍልሰት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የፖለቲካ ያለመረጋጋት ፈተናዎችን ደቅነዋል።

በአውሮፓውያኑ እስከ 2025 በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ውጤቶችን ማቀነባበር እስከ አልባሳትን ማምረት ድረስ ትኩረታቸውን አድርገው እንደሚከፈቱና ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ጠቀሜታን ማስገኘትን ዓላማቸው እንዳደረጉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃለላፊዎች ሲገልፁም ነበር።

ያስገኙታል ተብሎ ከሚታመነው ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ መካከል አንደኛው ቁጥሩ እየገዘፈ ለሄደው ወጣት የሥራ ዕድልን መፍጠር ነው።

ዕድሉን ለመጠቀም ተስፋ ከሚያደርጉት ወጣቶች መካከል የ19 ዓመቷ ቅድስት ደምሴ አንዷ ናት።

በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ሥራ ለመቀጠር ወደሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እያመራች በነበረችበት ወቅት ቢቢሲ ያናገራት ቅድስት ከምትፈልገው ሥራ ጋር የሚገናኝ ምንም ዓይነት የቀደመ ልምድ ባይኖራትም ፤ ቀጣሪዋ ስልጠና እንደሚሰጣት ግምት ይዛለች።

ሥራውን የምታገኘው በመቶዎች ከሚቆጠሩ በየዕለቱ ወደፓርኩ ከሚመጡ ሌሎች መሰል ሥራ ፈላጊዎች ጋር ተወዳድራ ነው።

ፈተናውን አልፋ ሥራውን ማግኘቱ ከተሳካላት በአነስተኛ ካፊቴሪያ ውስጥ ከነበራት የአስተናጋጅነት ሥራ በመጠኑ የተሻለ ገቢ እንደምታገኝ ትጠብቃለች።

ከዚህ ቀደም በፓርኩ ሥራ የጀመሩ ጓደኞቿ በወር 750 ብር እንደሚከፈላቸው ታውቃለች።

"ይች ብር ግን ምን አላት? ለኪራይና ለምግብ ስትባል ታልቃለች። መቼም እስከጊዜው ድረስ ነው" ትላለች።

እርሷም ሆነች ጓደኞቿ በፓርኩ ውስጥ ለመስራት የሚያስቡት ሌላ የተሻለ ሥራን እስኪያገኙ ድረስ ብቻ ነው።

"በዚያ ላይ ሥራው አድካሚ ነው።"ይላሉ።

ከክፍያ ማነስ ጋር የሚያያዝ የሠራተኞች ፍልሰት የሃዋሳ ሳይሆን የሌሎች የተገነቡም ሆነ በመገንባት ላይ ያሉ የኢንዱስትሪያል ፓርኮች አንድ ችግር እንደሆነ የሚያወሱት የመዋዕለ ነዋይ ባለሞያው አብዱልመናን መሃመድ ፓርኮቹ ከፍተኛ የሥራ ዕድልን መፍጠራቸው አይቀሬ ነው ይላሉ።

ሆኖም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የወጣቶች የሥራ አጥነት ዕድል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ መፍታት የማይታሰብ ነው ባይም ናቸው።

"የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እየተከፈቱ ያሉበት ሂደት ቀርፋፋ መሆን እንዲሁም ፓርኮቹ ከተከፈቱ በኋላ ተከራይተው ሥራ የሚጀምሩ ፋብሪካዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን የወጣት ሥራ አጥነት ቁጥርን የመቀነሱን ውጥን የሚያደናቅፍ ሆኗል።" የሚሉት አብዱልመናን "ስለዚህም ተመጋጋቢ ዕቅዶች ሊመተሩ ይገባል።" ይላሉ።

የተጋነነ ዕቅድቀርፋፋ አተገባበር

በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ሥራቸውን የጀመሩ አምራቾች ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ነፃ ውሃ እና የአስተዳደር አገልግሎት ያገኛሉ።

ጠቀም ያለ የግብር ፋታ የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ኪራዩም ረከስ ያለ መሆኑ ይነገራል።

የፓርኩ ግንባታ 250 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣ ሲሆን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ፍጥነት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ተሰርቶ መጠናቀቁን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይገልፃል።

እስካሁን ድረስ ሥራ የጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ ካሉት እና ይገነባሉ ተብለው ከታሰቡት አንፃር ዝቅተኛ ቁጥር ያለው እንደሆነ ልብ ማለት ይቻላል።

ተገንብተው የተጠናቀቁ የመንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በበላይነት በሚያስተዳድረው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሥር ያሉት ፓርኮች ሁለት ብቻ ናቸው።

ግንባታቸው ተጠናቅቆ ሥራ በጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ፋብሪካዎቻቸውን ያቋቋሙ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቢኖሩም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያስወጡትን ገንዘብ ከጠቀሜታቸው ጋር አነፃፅሮ ብያኔ ለማስቀመጥ ብሎም መፃኢ መልካቸውን ለመተንበይ የሚያስችል አጠቃላይ ጥናት ለማድረግ ዘለግ ያለ ጊዜ ወስዶ ፤ ውስብስብ የመዋዕለ ነዋይ መስፈሪያዎችን መመልከትን እንደመጠየቁ ያንን የማድረጊያ ጊዜው ገና እንደሆነ አቶ አብዱልመናን ይናገራሉ።

እንደዚያም ቢሆን የታሰቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሁሉ ይገነባሉ ብሎ ማመን ግን እንደሚከብዳቸው አይሸሽጉም።

"እጅግ የገዘፈ የገንዘብ እና የቴክኒክ ዕውቀት የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህንን በተተለመው የጊዜ ክልል ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል ነው።"ይላሉ።

ባለሞያው ኃሳባቸውን ለማጠናከር በአስረጅነት በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ አተኩረው በአውሮፓውያኑ እስከ 2025 ይሰራሉ የተባሉትን 17 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያነሳሉ።

ፓርኮቹን ለመገንባት 2.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ገንዘብ በሌሎች ዘርፎችም እንዲሁ ይገነባሉ ከተባሉት ሌሎች በርካታ ፓርኮች ጋር ሲደመር ፤ በየጊዜው የሚኖረው ግሽበት ከግምት ውስጥ ሲገባ ከመቶ ቢሊዮን የሚልቅ ብር የሚፈልግ ይሆናል።

የማኑፋክቸሪንግ መናኸሪያ?

በከፍተኛ ደረጃ የማኑፋክቸርኒንግ ዘርፍን ሲስብ የቆየው የእስያ ገበያ ርካሽ የሰራተኛ ጉልበት አምራቾችን የሚስብበት ገፅታው ሆኖ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጉልበት ዋጋ እየጨመረ መምጣቱን ተከተሎ አምራቾች ፊታቸውን ወደአፍሪካ ማዞር ይዘዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአህጉሪቱ የማኑፋክቸሪንግ መናኸሪያ ለመሆን ጠንከር ያለ ፍላጎት አላት።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ይህንን ፍላጎት ወደተግባር የመመንዘሪያ አንድ መንገድ ተደርገው ይጠቀሳሉ።

የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ባለፈው ዓመት በተመረቀበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት መሰረቱን የጣለ መሆኑን አስረግጠው አሞካሽተውት ነበር።

የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ 35 የፋብሪካ ማረፊያ አዳራሾች በተጨማሪ 15 አዳራሾችን መገንባት ያስፈለገው ኢንቨስተሮች ባሳዩት ፍላጎት መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይገልፃል።

የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስሪ ልማት ኢንስቲቲዩት በበኩሉ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ በሐዋሳ ኢንዱስሪያል ፓርክ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻዎች ምርቶቻቸውን ወደውጭ በመላክ በየወሩ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ እየተገኘ መሆኑን ገልፆ ነበር።

በወቅቱም ኢትዮጵያ በዘርፉ አገኘዋለሁ ብላ ተስፋ ካደረገችው ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሩብ ያህሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያመነጩታል ተብሎ እንደሚጠብቅ አብሮ ተገልጿል።

ሁሉም ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ ከ60000 በላይ ሠራተኞችን ይቀጥራል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል።

ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ሥራውን እንዲሠራ በማድረግ በየዓመቱ አንድ ቢሊየን ዶላር እንዲያመነጭም የማድረግ ዕቅድ አለ።

ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ለመሳብ ተደጋግመው ከሚሰጡ ቃል ኪዳኖች መካከል መካከል ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን የመሳሰሉ ልዩ ልዩ የማትጊያ እርምጃዎች፣ የልማት ብድሮች እንዲሁም የባቡር መንገድን ጨምሮ እየተስፋፋ ያለ የመሰረተ ልማት ግንባታ ይገኙበታል።

ርካሽ የሠራተኛ ጉልበትም አንደኛው ኢትዮጵያን ተመራጭ ያስደርጓታል ከሚባሉ እውነታዎች መካከል ይጠቀሳል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው መሆኑ እና ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው በተለየ ተመራጭ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ናቸው።

እነዚህ እርምጃዎች ወደፓርኮቹ ገብቶ ሥራ መጀመርን ቀላል እና ጊዜንም የሚቆጥብ ሒደት ያደርጉታል ተብሎ ከመታመኑ የሚወሰዱ ናቸው።

ሆኖም ኢትዮጵያ በዕቅድ የያዘቻቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በውጥኑ መሰረት ገንብታ ወደሥራ ማስገባት ብቸኛው የተደቀነባት ተግዳሮት አይደለም።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስኬት በግቢያቸው ውስጥ የሚገነቧቸው እና ፋብሪካዎችን የሚያስጠልሉ አዳራሾችን በሙሉ በማከራየት እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ላይ የሚመሰረት ነው።

ሥራ የጀመሩና በግንባታ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የገንዘብ እና የቴክኒካዊ ዕውቀት እጥረት ቢኖርባቸውም ተቀዳሚው ፈተና ግን ፖለቲካዊ እንደሆነ አብዱልመናን ይገልፃሉ።

"በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት እየወረራት ሲሆን ይህም ኢንቨስተሮች ስጋት እንዲገባቸው እና ከመምጣት እንዲቆጠቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።" ይላሉ

የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሌላኛው ሥራን የሚያስተጓጉል ምክንያት እንደሆነ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ሥራ አጥነት እና የስደተኞች ጉዳይ

አብዱልመናን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ አፍስሶ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በገፍ ለመገንባት ከመቻኮል በፊት አሁን የተገነቡት ፓርኮች የሥራ ሂደት እና የስኬት መጠን እንደአመላካች መውሰድን ይመክራሉ።

"በርካታ ፓርኮችን ከመገንባት በፊት፤ ባሉት ላይ ማተኮርና ለቀጣይ እርምጃዎች አጠቃላይ የሆነ ጥናትን ማከናወን ይሻላል።" የሚሉት አብዱልመናን ይህ ግን ሲከናወን እየተመለከቱ እንዳልሆነ አይሸሽጉም።

"እያየን ያለነው ለፈርጀ-ብዙው የምጣኔ ኃብት ችግራችን ሁሉንም ፈዋሽ መድኃኒት ናቸው በሚል እምነት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማከታተል ትኩሳት ነው።" ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለይ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ሊጠቀምበት እንደሚፈልግ ይናገራል።

በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ለስደተኞች የሥራ ዕድልን መፍጠር ወደአውሮፓ የሚደረግን ስደት ይቀንሳል በሚል እምነት 90000 ሰዎችን ይቀጥራሉ ብሎ ላመነባቸው ሁለት ፓርኮች ግንባታ 500 ሚሊዮን ዶላር ለመለግስ ቃል ገብቷል።

የአውሮፓ ኅብረት ያለበትን ከስደት ጋር የሚያያዝ ችግር ለመቅረፍ ሲል ለኢትዮጵያ የለገሰው ገንዘብ ኢትዮጵያ በሽህዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ሥራን እንድትፈጥር የሚጠይቃት ነው።

አብዱልመናን ግን ይህን ውሳኔ በጥልቅ ልትፈትሸው ይገባል ባይ ናቸው። "ኢትዮጵያ ጠናን የሆነ የራሷ የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር አለባት።"ይላሉ።