ቤተሰቦች ዘመድ ወዳጆቻቸውን ፍለጋ ላይ ናቸው

የመንገደኞች ቤተሰብ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የመንገደኞች ቤተሰብ በሃዘን ውስጥ ሆነው ስለቤተሰቦቻቸው መረጃ እየጠበቁ ነው።

ባለቤትነቱ የአሴማን አየር መንገድ የሆነው እና የበረራ ቁጥር EP3704 ከቴህራን ያሱጃ ሲበር የነበረ ሲሆን ትናንት እሁድ ዛጋሮስ በተባለ ተራራማ ቦታ ተከስክሶ 66 ተሳፋሪዎች በሙሉ ሳይሞቱ አይቀርም ተብሏል።

በኢራን መዲና ቴህራን ዋና መቀመጫውን ያደረገው ይህ አየር መንገድ፤ ATR 72-500 የተባለውን ጣሊያን እና ፈረንሳይ ሰራሽ ባለሁለት ሞተር አውሮፕላን የተከሰከሰበት ምክንያት አልታወቀም።

በአካባቢው የነበረው ከባድ ንፋስ እና በረዷማ የአየር ንብረት ፍለጋውን አስተጓጉሎት ነበር።

እንደ የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ አውሮፕላኑ ወደ መዳረሻው ለመድረስ 22 ኪ.ሜ ብቻ ነበር የቀረው።

Image copyright Mehrad Watson
አጭር የምስል መግለጫ ATR 72-500 አውሮፕላን ጣሊያን-ፈረንሳይ ሰራሽ እንደሆነ ተነግሯል።

የኢራን ሲቪል አቪዬሽን አውሮፕላኑ የ25 ዓመት እድሜ እንዳለው ገልጾ ከ66 ተሳፋሪዎች መካከል ሁለት አብራሪዎች እና ሁለት የበረራ አስተናጋጆች ይገኙበታል።

የመንገደኞች ቤተሰቦች ቴህራን አየር መንገድ አቅራቢያ በሚገኝ መስጅድ ተሰባሰበው ይገኛሉ።

ባለቤቷን በአደጋው ያጣች ሴት ''እየሆነ ያለውን ነገር ማመን አልችልም''ብላለች።

አንድ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በረራው አምልጦት ከአደጋው የተረፈ ሰው ይዞ ወጥቷል።

ይህ ግለሰብ ያልተገለገለበትን የአውሮፕላን ቲኬት በማሳየት''ፈጣሪ እጅግ ይወደኛል ሆኖም ግን በአደጋው ህይወታቸውን ላጡት እጅግ አዝኛለው'' ብሏል።

በቅርብ ዓመታት በኢራን ተደጋጋሚ የአውሮፕላን አደጋዎች እየተከሰቱ ሲሆን ኢራን አድሜያቸው የገፉ አውሮፕላኖችን ትጠቀማለች።

የኢራንን የኒኩሌር ፕሮግራም ለማስቆም ታስቦ የተጣለው ማዕቀብ አውሮፕላኖችን ለመጠገን የሚያስፈልጓትን መለዋወጫዎች ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል።