በናይጄሪያ ሴት ተማሪዎች የቦኮ ሃራምን ጥቃት አመለጡ

ቦኮ ሃራም

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ቦኮ ሃራም በሰሜናዊ ናይጄሪያ እስላማዊ መንግሥት መመስረት ይፈልጋል

በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ አንድ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች እና መምህራን የቦኮ ሃራምን ጥቃት ማምለጣቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ።

የዓይን እማኞች እንዳሉት ከሆነ የቦኮ ሃራም ወታደሮች ሰኞ ጠዋት ዳፕቺ በምትባል ከተማ ከደረሱ በኋላ ተኩስ ከፈቱ እንዲሁም ፈንጂዎችን ማፈንዳት ጀመሩ።

የፍንዳታውን ድምጽ ቀድመው የሰሙት ሴት ተማሪዎች እና መምህራን ቦኮ ሃራም ወደ ትምህርት ቤታቸው ከመድረሱ በፊት በማምለጣቸው የጥቃቱ ሰለባ ከመሆን ተርፈዋል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ቦኮ ሃራም በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ከምትገኝ ቺቦክ ከተማ 270 ሴቶችን አፍኖ ወስዶ ነበር።

የዳፕቺ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በትምህርት ቤቱ የሚገኙትን ሴቶች ለማፈን ነበር የመጡት ብለዋል።

ታጣቂዎቹ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲደርሱ ባዶ ሆኖ በማግኘታቸው በህንጻዎቹ ውስጥ ያገኙትን ከዘረፉ በኋላ አውድመው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።

የናይጄሪያ ጦር በተዋጊ ጄቶች በመታገዝ የአጸፋ እርምጃ ወስዷል ተብሏል።

ባሳለፍነው ግንቦት ወር ከቺቦክ ታፍነው ከተወሰዱት መካከል 100 ሴት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል።

ብዙዎቹ የተለቀቁት መንግሥት የቦኮ ሃራምን 5 ኮማንደሮች ከእስር ለመልቀቅ ከተስማማ በኋላ ነበር።

ይሁን እንጂ አሁንም 100 ሴት ተማሪዎች በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።

ላለፉት ስምንት ዓመታት ቦኮ ሃራም በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ሲፈጽማቸው በቆየው ጥቃቶች ወደ አስር ሺ የሚጠጉ ንጹሃን ህይወታቸውን አጥተዋል።