በሞዛምቢክ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 17 ሰዎች ሞቱ

የሞዛምቢክ ቆሻሻ ክምር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

የአካባቢው ባለስልጣናት በቆሻሻ መጣያ ስፍራው በቁጥር ምን ያህል ነዋሪዎች እንዳሉ አናውቅም ብለዋል።

የሞዛምቢክ ዋና ከተማ በሆነቸው ማፑቶ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 17 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁስላቸውን የአከባቢው ባለስልጣናት ተናገሩ።

ሰኞ ጠዋት በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ 15 ሜትር ቁመት ያለው የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ነው ጉዳቱ የደረሰው።

የቆሻሻ መጣያ ስፍራው በከተማዋ የሚገኙ የድሆች መኖሪያ ሲሆን፤ በቆሻሻ ክምሩ ላይ ከላስቲክ ከተሰሩ ዳሶች ውስጥ ይኖሩ ነበር።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተጎጂዎችን በመፈለግ ላይ ናቸው።

የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ቃለ አቀባይ ሊዮናደል ፔሌምቤ የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

''ከአካባቢው ባለስልጣናት መረዳት እንደቻልነው፤ በአካባቢው ይኖራሉ ተብለው የሚገመቱት ከሟቾች ቁጥር በላይ ናቸው'' ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተጎጂዎችን በመፈለግ ላይ ይገኛሉ

የቆሻሻ መጣያ ስፍራው ከ40 ዓመታት በለይ በአካባቢው እንደነበር ይነገራል። የክረምት ወራት ሲቃረብ የአካባቢው ባለስልጣናት በቆሻሻ መጣያ ስፍራው ላይ የሚኖሩትን ዜጎች በማስነሳት ወደ ሌላ ቦታ ያዘዋውሯቸዋል።

ይሁን እንጂ የክረምቱ ወራት እነዳለፉ ነዋሪዎቹ ተመልሰው በቆሻሻ ክምሩ ላይ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ ሲሉ የአከባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

የሞዛምቢክ መንግሥት የቆሻሻ መጣያ ስፍራውን ሙሉ ለሙሉ እዘጋዋለሁ ቢልም እስካሁን ግን ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል።