በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመድሃኒት ስህተቶች እየተፈጠሩ ነው

Drugs Image copyright Getty Images

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመድሃኒት ስህተቶች እየተፈጠሩ መሆኑን አንድ ጥናት አስታወቀ።

በጥናቱ መሰረት ከፍተኛ አደጋ እና ሞት እያስከተሉ መሆኑን እንግሊዝ የጤና ሚንስትር ጀርሚ ሃንት ገልጸዋል።

የጤና ተቋማት በየዓመቱ 237 ሚሊዮን ስህተቶችን እየፈጠሩ ሲሆን ይህም ከሚሰጡ አምስት መድሃኒቶች በአንዱ ስህተት ይፈጠራል እንደማለት ነው።

እንደጥናቱ ከሆነ ስህተቱ በአብዛኛው ችግር ባይፈጥርም አንድ አራተኛ የሚሆነው ግን አደጋ አስከትሏል።

ስህተቶቹ ከ22ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሞቶችም ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ጥናቱን ያካሄዱት የማንቸስተር፣ የሼፊልድ እና ዮርክ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉት በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ ባለመኖሩ በቀደምት ጥናቶች ላይ ተመሰረተ ግምት ወስደዋል።

ሆኖም ማስጠንቀቂያ ለመስጠት በቂ ሆኖ አግኝተውታል።

ከሚፈጠሩት ስህተቶች መካከል፡

  • የተሳሳተ መድሃኒት መስጠት
  • የተሳሳተ መጠን መስጠት
  • ህክምና ለመስጠት መዘግየት
Image copyright Other
አጭር የምስል መግለጫ ሌላ ታካሚ መድሃኒት በስህተት የተሰጣቸው ካትሪን ያንግ እና አናታቸው ኢሪን

አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ስህተቶች ከሆስፒታል እንክብካቤ ጋር የሚያያዙ ሲሆን እንደምሳሌ የተጠቀሰው በቀዶ ህክምና በፊት ከማደንዘዣ ጋር የተገናኘ ስህተት ነው።

በመድሃኒት ስህተት ችግር ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል የካትሪን ያንግ እናት የሆኑት ኢሪን ይገኙበታል።

የመድሃኒት ማዘዣቸው ከሌላ ሰው ጋር በመቀላቀሉ ምክንያት ለሳምንታት በስህተት ብዙ መድሃኒቶችን ወስደዋል።

ይህን ተከትሎም በትከሻቸው፣ አንገታቸው እና አይናቸው ላይ ህመም አጋጥሟቸዋል።

ስህተት መፈጸሙን ህክምና ባለሙያዎች ሊያውቁት አለመቻላቸውን ልጃቸው ገልጸዋል።

"ምንም የህክምና ትምህርት የሌለኝ ሰው ነኝ ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠሁት" ብለዋል።

"በጊዜ ችግሩ ላይ ብንደርስበትም ሌሎች በዚህ በኩል እድለኛ አይደሉም" ሲሉ ያንግ አስረድተዋል።

ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆሙት ሃንት ችግሩ ዓለም አቀፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ከሚታሰበው በላይ ትልቅ ችግር ነው። መከላከል እየተቻለ ግን ፍተና ችግር እና ሞት እያስከተለ ነው።" ብለዋል።

ስህተቶቹ ላይ ግልጽነት ኖሮ ለወደፊት ትምህርት ሊወሰድባቸው ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች