"ልጆች እያሳደጉ ትምህርት ከባድ ቢሆንም፤ ፍላጎቱ ካለ ሁሉንም ይቻላል"

ነፃነት ከቤተሰቧ ጋር

ከ20 ዓመት በፊት ነበር በስደት ለንደን የገባችው የአራት ልጆች እናት፣ ኤርትራዊት መምህር ነፃነት ንርዓዮ።

መምህርት ነፃነት ልጆቿን ለማሳደግ ለ12 ዓመታት ትምህርቷን አቋርጣ ነበር። በ2014 በለንደን ዩኒቨርሲቲ ሳዉዝ ባንክ ያቋረጠችዉን ትምህርት ቀጥላ በዲግሪ ተመረቀጭ። ዓለምአቀፍ እውቅና የሚያሰጣትን ብቃት ለማግኘትም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየወሰደች ነው።

"ወደዚህ ሃገር እንደመጣሁ የበረራ አስተናጋጅ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። ለዚህም ለሦስት ዓመት ተምሬ በአንድ የጉዞ ወኪል ሥራ ጀመርኩኝ። በኋላ ላይ ግን ድርጅቱ ከስሮ ስለተዘጋ ትዳር መስርቼ ልጆቼን ማሳደግ ጀመርኩኝ" ትላለች።

ልጆቿን በምታሳድግበት ወቅት መጽሐፍት ታነብላቸው ስለነበር ቆይታ መምህር ለመሆን ፍላጎት እንዲያድርባት ምክንያት ሆነ። ለዚህም ወደ ኮሌጅ በመሄድ ረዳት መምህር ለመሆን የሚያግዛትን ሥልጠና ለአንድ ዓመት ወሰደች።

"ትምህርቴን እንደጨረስኩ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ለስድስት ወራት ረዳት መምህር ሆኜ ሠራሁ። አሁን በማስተምርበት ትምህርት ቤት ለ12 ዓመታት ረዳት መምህር ሆኜ ሠርቻለሁ" ትላለች ነፃነት።

ከዚህ ባለፈ ለሙያ ካላት ፍቅር በተጨማሪ የሚጠበቅባት ደረጃ ላይ ለመድረስ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ትምህርቷን ተከታትላለች።

"ቀላል አልነበረም። ልጆች እያሳደጉ ትምህርት ከባድ ቢሆንም፤ ፍላጎቱ ካለ ሁሉም ይቻላል" ባይ ናት ነፃነት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንዴት ተወጣችው?

"ጠዋት 12 ሰዓት ተነስቼ ልጆቼን አሰናዳለሁ። ልጆቼ ከትምህርት ቤት ተመልሰው የቤት ሥራቸዉን ሠርተዉ ሲጨርሱ፤ እኔ ደግሞ ማታ አምሽቼ እተኛለሁ። የእንቅልፍ ሰዓት ሲያጥረኝ አስታውሳለሁ። የነገዋ ተስፋ ቀድማ ትታየኝ ስለነበር ያጣሁት የሚመስለኝ ነገር አልነበረም" ስትል ያላትን ጊዜ እንዴት እንደምታሳልፍ ትናገራለች።

ነጻነት በተለይ ስደት ላይ ለሚኖሩ ሴቶች እንዲህ ትላለች "ሁሉም እንደሚቻል ማመን ዋናው ነገር ነው። ይቻላል ብሎ መሥራት ብቻ በቂ ነው ባይ ነኝ'' የምትለዉ ነፃነት በመቀጠል "ለጥረቴ መሳካት ከጎኔ ያልተለየኝን ባለቤቴን ጴጥሮስ ዘካርያስን አመሠግነዋለሁ፤ ከዚህም ተነስቼ ሁሉም ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲያግዙ ለመምከር እፈልጋለሁ" ብላለች።