ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚደረግ ውይይት ከኒውክሌር መሳሪያ ጋር ተገናኘ ነው- አሜሪካ

South Korea's President Moon Jae-in (L), his wife Kim Jung-sook (C), US White House adviser Ivanka Trump

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የሰሜን ኮሪያ ጄነራል እና ኢቫንካ ትራምፕ በአንድ አካባቢ ተቀምጠዋል

ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚደረግ የትኛውም ውይይት የመጨረሻ ግቡ ኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ማደርግ ነው ስትል አሜሪካ አስታወቀች።

በፒዮንግቻንግ የክረምት ኦሊምፒክ ማጠቃለያ ላይ ሰሜን ኮሪያ ለውይይት ዝግጁ መሆኗን ማስታወቋን ደቡብ ኮሪያ ገልጻ ነበር።

ቀደም ሲል ሰሜን ኮሪያ ለውይይት ለመቅረብ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደማትቀበል ይፋ አድርጋለች።

"ፒዮንግያንግ ውይይት ለማድረግ የመዘጋጀቷ መልዕክት ሃገሪቱን የኒውክለር ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጠጥረት የሚያበቃበት የመጀመሪያ ጉዞ ስለመሆኑ ወደ ፊት እናያልን" ብላለች አሜሪካ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ለውይይት ዝግጁ መሆኗን የገለጸችው ከክረምቱ ኦሊምፒክ መጠናቀቅ በፊት ባለስልጣናቷ ከደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው።

በውድድሩ የመዝግያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ፤ ከሰሜነ ኮሪያው ተወካይ ጄኔራል ኪም ዮንግ-ቾል አቅራቢያ ቢቀመጡም ውይይት እንደማያደርጉ ታውቋል።

ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሙን ጃይ-ኢን ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Pool

የምስሉ መግለጫ,

በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ ማይክ ፔንስ ከሰሜን ኮሪያው ተወካይ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር

ሃገሪቱ "የሁለቱ ኮሪያዎች እና የሰሜንና የአሜሪካ ግንኙነት በጋራ እንዲጎለብት ትፈልጋለች" ብሏል ጽህፈት ቤቱ። ይህ ከመገለጹ ከሰዓታት በፊት በዋሽንግተን ይፋ የተደረገው አዲስ ማዕቀብ "ጦርነት ቀስቃሽ ነው" ስትል ሰሜን ኮሪያ አስታውቃ ነበር።

የሰሜን ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱን ኮሪያዎች በኦሊምፒኩ ያደረጉትን መተባበር አድንቆ አሜሪካ ግን "በአዲሱ ማዕቀብ ሳቢያ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ የጦርነት ስጋትን ፈጥራለች" ብሏል።

ሁለቱ ኮሪያዎች ከአውሮፓዊያኑ 1950-53 ጦርነት በኋላ የተከፋፈሉ ሲሆን ከዚያ በኋላም የሠላም ስምምነት አልተፈራረሙም።

ባለፈው ዓመት ሰሜን ኮሪያ ያደረገቻቸውን የኒውክለር እና የሚሳኤል ሙከራዎች ተከትሎ አሁን ያለው ሁኔታ የአካባቢውን ውጥረት ሊያስቆም አይችል ይሆናል ሲሉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን አስቀምተዋል።