ደቡብ አፍሪካ፡ ራማፎሳ አዲሱን ካቢኔያቸውን ይፋ አደረጉ

South Africa's deputy President Cyril Ramaphosa Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሲሩል ራማፎሳ ጃኮብ ዙማን በመተካት ነው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት

አዲሱ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ካቢኔያቸውን ይፋ አደረጉ።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከቦታቸው ተነስተው የነበሩትን ንህላንህላ ኔኔን በድጋሚ የገንዘብ ሚንስትር አድርገው ሾመዋል።

ተደጋጋሚ የሙስና ክስ የቀረበባቸው ዙማ በፓርቲያቸወ ግፊት ከስልጣን እንዲለቁ መደረጋቸው ይታወሳል።

"አዲስ ምዕራፍ" ይከፈታል ሲሉ ቃል የገቡት ራማፎሳ ሙስና ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

"ይህንን ለውጥ ሳደርግ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እና ፈጣን ትራንስፎርሜሽን እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት አስገብቻለሁ" ብለዋል ራማፎሳ ካቢኔያቸውን ፕሪቶሪያ ውስጥ ይፋ ሲያደርጉ።

አብዛኛዎቹን የቀድሞ ሚንስትሮች ቦታን ያልነኩት ራማፎሳ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች ናቸው ያሏቸውን ተወሰኑትን ከስልጣናቸው ዝቅ ሲያደርጉ ሌሎቹን ያለሥራ አስቀርተዋል።

የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካዊያን ብሔራዊ ምክር ቤት (ኤኤንሲ) ፓርቲ ምክት የሆኑትን ዴቪድ ማቡዛን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ሾመዋል።

በፓርቲው የሊቀ-መንበርነት ምርጫ ወቅት ያሸነፏቸውን የዙማን የቀድሞ ባለቤት ንኮሳዛና ድላሚኒ-ዙማን ሚንስትር አድርገው ተሹመዋቸዋል።

ትልቁ ዜና ሚያዝያ ላይ ከፋይናንስ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ንህላንህላ ኔኔን በድጋሚ መሾማቸው ነው። በወቅቱ ውሳኔውን በብዙዎች ዘንድ ተተቸ ሲሆን፤ ባለሃብቶችም በሃገሪቱ መዋለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ ስጋት ፈጠረ ነበር። በወቅቱ የሃገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሪ በታሪኩ ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።

ራማፎሳ ባለፈው ሳምንት ለሃገሪቱ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክ ዋነኛ ሥራቸው ሙስናን መዋጋት፣ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ እና የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሆነ አስታውቀው ነበር።

ዙማ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዘጠኝ ዓመታት ተደጋጋሚ የሙስና ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ሃገሪቱም በከፍተኛ የውጭ ዕዳ እና እና በሥራ አጥነት ችግር ውስጥ ነበረች።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ