ኤኤንሲ ያለ ካሳ የነጮችን መሬት የመንጠቅ ሃሳብን እንደሚደግፍ አስታወቀ

ጂሊየስ ማሌማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካው ገዥ ፓርቲ ኤኤንሲ በነጮች የተያዘን መሬት ያለካሳ መውሰድን በሚመለከተ ፅንፈኛው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓርቲ ያቀረበውን ሃሳብ እንደሚደግፍ አስታውቋል።

ከትናንት በስቲያ ጉዳዩን በሚመለከት በፓርላማ የተደረገውን ክርክር ሲመሩ የነበሩት የኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓርቲ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ነበሩ።

"የእርቅ ጊዜ አብቅቷል። አሁን ጊዜው የፍትህ ነው። የነጮች መሬት ተወስዶ ለፍትሃዊ ክፍፍል መቅረብ አለበት"ብለው ነበር።

ጁሊየስ ማሌማ በደቡብ አፍሪካ የቅኝ አገዛዝ አስተዳዳሪ፤ የኬፕታውን መስራችና የነጮች ሰፈራ አስተባባሪ የሆኑትን ጃን ቫን ሪቢክን በመጥቀስም "የልጅ ልጆቹ መሬታችንን እንደምንፈልግ ካልተረዱ ነገሩ እዚያ ላይ ያበቃል። ይህ ከክብራችን በላይ የሆነ ነገር ነው" ብለዋል።

በፓርላማው ክርክር የኤአንሲ ፓርቲም የውሳኔውን ሃሳብ እንደሚደግፈው አስታውቋል።

የውሃና የንፅህና ሚኒስትሩ ጉግሌ ክዊንቲም ለውሳኔ ሃሳቡ መፅደቅ ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

"መሬት ያለምንም ካሳ ከነጮች መወሰድ አለበት የሚለውን ሃሳብ ኤኤንሲ በሙሉ ልብ ይደግፋል" ሲሉም አክለዋል።

የአገሪቱ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው ዲሞክራቲክ አሊያንስ ቡድን ግን ያለ ካሳ የነጮችን መሬት መውሰድ መፍትሄ እንደማያመጣ እያስጠነቀቀ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ላይ በደቡብ አፍሪካ የተደረገ የመሬት ምዝገባ እንደሚያሳየው 72 በመቶ የሚሆነው የእርሻ መሬት ዛሬም በነጮች እንደተያዘ ነው። ቀጥሎ ደግሞ 15 በመቶ የሚሆነው ቅልቅል ዝርያ ባላቸው ሲሆን አምስት በመቶ የሚሆነው በህንዶች የተያዘ ነው። ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን የያዙት የእርሻ መሬት አራት በመቶ ብቻ ነው።