ግብጻዊቷ ዘፋኝ አባይ ላይ ቀልደሻል ተብላ እስር ተፈረደባት

Egyptian singer Sherine Abdel Wahab

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ሼሪን በጣም ታዋቂ ግብጻዊት ዘፋኝ ናት

ግብጻዊቷ ዘፋኝ ሼሪን አብድል ዋህብ በአባይ ወንዝ ንጽህና ላይ በመቀለዷ ለስድስት ወራት በእስር እንድትቆይ ተፈረደባት።

በግብጽ ታዋቂ ከሆኑ ዘፋኞች አንዷ የሆነችው ሼሪን ለአድናቂዎቿ ከወንዙ ውሃ መጠጣት በፓራሳይት እንዲጠቁ ሊያደርጋቸው እንደሚቸል ገልጻላቸዋለች።

"ይልቅ ኤቪያን የተባለውን የታሸገ ውሃ ጠጡ" ብላ ቀልዳለች።

ላይላ አሜር የተባለች ሌላ ዘፋኝም በአንድ የሙዚቃ ቪዲዮዋ ምክንያት ባለፈው ማክሰኞ የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶባታል።

የሼሪንን ያህል ታዋቂነት የሌላት አሜር "መጥፎ ተግባር እና ለሥነ-ምግባር ተቃራኒ የሆነ መልዕክት አስተላልፋለች" በሚል ነው ጥፋተኛ የተባለችው። የሙዚቃ ቪዲዮው ዳይሬክተር እና ሌላ ተዋናይም እስር ተፈርዶባቸዋል።

ካይሮ የሚገኝ ፍርድ ቤት ነው ሼሪንን ሃሰተኛ ዜና በማሰራጨት የፈረደባት። ጉዳዩ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅም የዋስትና ገንዘብ አስይዛ ነጻ መሆን እንደምትችል አህራም የተባለው ሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

ሼሪን 'ማሽረብቴሽ ሜን ኒልሃ' (ከአባይ ወንዝ ጠጥተዋል?) የሚለውን ዘፈን እንድትዘፍን ስትጠየቅ የሚያሳይ ቪዲዮ ከተለቀቀ በኋላ ነበር ባለፈው ህዳር ክስ የተመሰረተባት።

"ከአባይ ውሃ መጠጣት በቢልሃርዚያ በሽታ እንድጠቃ ያደርገኛል" ብላ መልሳለች።

ከተመሰረተባት ክስ በተጨማሪ የግብጽ ሙዚቀኞች ማህበር "በግብጽ ላይ በመቀለዷ ምክንያት" ሥራዎቿን እንዳታቀርብ ማገዱን አስታውቋል።

ሼሪን በኮንሰርቱ ላይ "ለማይገባው ቀልዷ" ይቅርታ የጠየቀች ሲሆን፤ ስለጉዳዩ የተናገረችው ከአንድ ዓመት በፊት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ መሆኑን ጠቁማለች።

"ውዷ ሃገሬ ግብጽ እና የግብጽ ልጆች ላይ ለፈጠርኩባችሁ ቁስል በሙሉ ልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብላለች።

የቢልሃርዚያ በሽታ በግብጽ ታሪክ ውስጥ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን በሽታው ለብዙ ሺህ ዓመታት እንዳይበላሹ ተደርገው በተቀመጡ አስከሬኖች ውስጥም ተገኝቷል።

ሆኖም ግን ባለፉት አስር ዓመታት በተደረገ የጤና ፕሮግራም ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ተችሏል።