ከባድ ክረምት አውሮፓን እየፈተነ ነው

Europe

ከባድ ክረምትና ከፍተኛ በረዶ በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሃገራት የዜጎችን የዕለት ተለት ኑሮ ከባድ አድርጎታል።

የአየር ንብረቱ በዚህ መልክ መክበዱ በርካታ ቀውሶችን እያስከተለም ነው። በከባድ ዝናብና በረዶ መንገዶችና ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎችም ተሰርዘዋል።

በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአየር ፀባይ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሞቶች በርክተዋል። ለምሳሌ በፖላንድ ይህ ቁጥር ከ21 ወደ 55 ጨምሯል።.

የዓለም ጤና ድርጅትም ድሆች በተለይም የጎዳና ተዳዳሪዎችና ስደተኞች በቅዝቃዜው ሊጎዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

"ከቅዝቃዜ ጋር ተያያዥ በሆኑ ህመሞች የሚጠቁት፤ በተለይም አዛውንቶች፣ ህፃናትና ከባድ ህመም ያለባቸው ናቸው" ይላል የዓለም ጤና ድርጅት መግለጫ።

ይህ የወቅቱ የአየር ፀባይ በአየርላንድ ላለፉት አስር ዓመታት ያልታየ ነው።

ከደብሊን አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የሚደረጉ በረራዎች ተስተጓጉለዋል።

በተመሳሳይ የጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ ሃሙስ እለት በበረዶ ክምር ምክንያት ተዘግቶ ነበር።

በፈረንሳይ ሞንትፒለር ከተማ 2000 የሚሆኑ አሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ አልቻሉም።

በረዶ በቀላቀለ ንፋስ የተመታው የአምስተርዳሙ አውሮፕላን ማረፊያም በረራዎቹን ለመሰረዝ ተገዷል።

በእንግሊዝም በበረዶ የተያዙ ተሽከርካሪዎችን ለማስለቀቅ ወታደራዊ ኃይሎች ሊሰማሩ ግድ ሆኗል።