'የወር አበባ ላይ ስለነበርኩ ለአያቴ ሐዘን መቀመጥ አልቻልኩም'

የሜጋ ሞሃ አያት
አጭር የምስል መግለጫ የሜጋ ሞሃ አያት

በብዙ የሕንድ ቤተሰቦች ውስጥ የማይዳሰስ ርዕስ ቢሆንም እንኳን የወር አበባ በሜጋ ቤተሰብ ውስጥ ግን ነውር አልነበረም። አንድ ቀን የዚህ እውነት ተቃራኒ በሁሉም ዕድሜ ክልል ያሉ ቤተሰቦቿ በተሰባሰቡት ወቅት ያለውን ልዩነት ገሃድ አወጣ።

ከመታጠቢያ ቤት እየወጣች "ታምፖን (የወር አበባ መጠበቂያ አይነት) ያለው ሰው ይኖራል?" ብላ ጠየቀች።

በትኩስ ሻይ ዙሪያ ጨዋታ ይዘው የነበሩት ብዙው የቤተሰቧ አባላት በአንድ ጊዜ ፀጥ አሉ። በሕንድ ደቡብ ያለችው ከታሚል ናዱ ወጣ ብላ የምትገኘው ራሜስዋራም የተሰኘችው ደሴት ላይ በአንድ የሆቴል ክፍል ነበር የታጨቁት።

ተፈጠሯዊ ያልነበረው ፀጥታ በሁለት ምክንያቶች በጣም ያስታውቅ ነበር። አንደኛ ዝናቡ መስኮቱን ይደበድብ ስለነበርና ሁለተኛ ደግሞ በሦስት የተለያዩ አህጉራት ላይ የሚኖሩት ቤተሰቦቿ በየቀኑ ዋትሳፕም ላይ እየተገናኙ በአካል ሲገናኙ ግን መቼም ፀጥታ ባለመስፈኑ ነው።

በሆቴሉ አልጋ ላይ ጋደም ብላ የነበረችው አክስቷ ተነስታ የእጅ ቦርሳዋን አነሳች። የወር አበባ መጠበቂያ አወጥታ አቀበለቻት።

"ይህ ፋርማሲ እስክንሄድ ድረስ ይጠቅምሻል'' አልችና ባዘነ ፊት እያየቻት ''ይህ ምን ማለት እንደሆነ ታውቅያለሽ አይደል?'' ብላ ጠየቀቻት።

ሜጋ ግን አላወቀችም ነበር።

"ቤተ-መቅደስ መምጣት አትችይም ማለት ነው'' አለቻት።

Image copyright Vidya Nair
አጭር የምስል መግለጫ በራሜስዋራም ያለው የፀበል ገንዳዎች ሰዎች በመጠመቅ ለቅድመ ዘር አክብሮት የሚያቀርቡበት ነው

ቤተሰባቸው ለእረፍት አልነበረም ወደ ራሜስዋራማ ያቀናው። ይህች ደሴት በጎብኚዎችና በዓሣ አስገሪዎቿ የታወቀች ብትሆንም እነርሱ ግን የተሰባሰቡት ለአሳዛኝ ጉዳይ ነው።

ሜጋ የምትወዳት አያቷ ካረፈች ዓመት ሆኗት ነበር። እሷው ነበረች በተለያዩ አህጉራት ላይ ያሉትን የቤተሰቡ አባላትን የምታሰባስበው።

ባለፈው ታህሳስ የህልፈቷ ዜና ሲደርሳቸው ሁሉም በፍጥነት አውሮፕላን ተሳፈሩ።

እንደየአካባቢው ቢለያዩም በሒንዱ ባህል በሞት ዙሪያ ብዙ ወጎች አሉ።

ሰው ሲሞት የሜጋ ቤተሰብ የሕንድ ደቡብ ሒንዱ ባህልን ነው የሚከተለው። አስክሬኗን ቤታቸው ወስደው በነጭ ጥጥ ከገነዙ በኋላ በትልቅ ኮባ ላይ አስተኝተው ተሰብስበው ፀለዩ። ወንዶቹ አስክሬኑን ለማቃጠል ሲወስዱ ሜጋም አብራ ብትሄድ ትወድ ነበር።

ካረፈች በኋላ ለ15 ቀናት ሥጋ አልበሉም ነበር። ከ90 ቀናት በኋላ ደግሞ ልዩ ዝግጅት አደረጉ።

ኤርፖርትም እርስ በርሳቸው ተሰነባበተው ለቀጣዩ የሞት ባህል በራሜስዋራም እንደሚገናኙ ቃል ገቡ።

እዚያም ነበር የሜጋ ወንዱ አያት ከሴት አያቷ ቀድሞ የዛሬ 36 ዓመት ሲሞት አያቷ የመጨረሻዎቹን ሥነ-ሥርዓቶች ያስከበረችው።

በቤንጋል ዉሃ ዳርቻ ላይ ያለው ራሜስዋራም ለታሪካዊ ቤተ-መቅደሶቹ የታወቀ ነው። አፈ ታሪኩ እንደሚለው 'ራማ' የተሰኘው የሒንዱ አምላክ እዚያ ነበር 'ሲታ' የተሰኘችውን ሚስቱን ከጠላፊዋ ለማስፈታት ድልድይ ወደ ሽሪላንካ የሠራው።

በሦስቱ የአውሮፕላን ጉዞዎች መካከልና በሚያንገጨግጨው የመኪና ጉዞ እንዳነበበችው ራሜስዋራም በወሳኝ ጊዜያት ነበር የሚኬደው። ሜጋም እራሷን እንደ ሐይማኖታዊ ሰው ቆጥራ ባታውቅም ግን አሁን ከሚጓዙት ሰዎች መካከል አንዷ ሆና እራሷን አግኘችው።

Image copyright Vidya Nair
አጭር የምስል መግለጫ ታሚል ናዱ ታዋቂ የሐይማኖታዊ ጉዞ ስፍራ ነው

አያቷ በሞተች በቀጣዮቹ ወራት በራሜስዋራም የሚደረገው የመሰናበቻው የመጨረሻ ምዕራፍ ምን እንደሚመስል ብዙ ታስብ ነበር።

በአክስቷ የሆቴል ክፍል ውስጥ ሆነው ለሞተችው አያቷ የመሰናበቻ የመጨረሻው ክፍል ላይ መገኘት እንደማትችል ሲነገራት ሜጋ እራሷን የመከላከል ስሜት ውስጥ ገባች።

ሜጋ በፍጥነት ''በወር አባበዬ ላይ ስላለሁኝ ነው ቤተ-መቅደስ መሄድ የማልችለው?'' ብላ ጠየቀች።

አይኖቿን ቀስ ብላ በማጥበብ አክስቷ የሜጋ አነጋገር በወጣትነቷ ተቀባይነት እንዳልነበረውና አሁን ደግሞ ይበልጥ እንደሌለው በሚገባት መልኩ አየቻት።

ሜጋም ወዲያውኑ ''ይቅርታ'' አለቻት። ''ግን እርግጠኛ ነን ይህንን አይደለም እያልሽኝ ያለሽው። ይህን ሁሉ ሃገር አቋርጬ አብሬያችሁ ቤተ-መቅደስ ላልገባ አይደለም መቼስ'' አለች።

አክስቷም ''እኔ እኮ አይደለሁም ይህን የምልሽ። እንደዚያ ስለሆነ ነው'' አለቻት።

''ማን ስላለ'' ብላ ሜጋ አጥብቃ ጠየቀቻት።

''እንዲህ ነው በቃ። ትልቅ ነገርም ነው'' ብላ ሜጋን ለማገዝ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ አድርጋ ንግግሩን ቋጨችው። ውሳኔውም ፀደቀ።

ከሹፌሩ ጋር በቤተ-መቅደሱ ደጃፍ ትጠብቃለች።


ልጅ እያለች የወር አበባዋ ሲመጣ የተለያዩ ምክንያቶች እየተነገሯት ቴምፕል ከመሄድ ትታቀብ ነበር።

አንድ አክስቷ ይህ የመጣው በድሮ ጊዜ እንደዛሬ የወር አበባ መጠበቂያ ስላልነበራቸው ነው ብላ ነግራታለች። እናቷ ደግሞ በወር ውስጥ ይህን ቀን ብቻ ነው ሴት ልጅ ከሁሉም ሥራ የምትታቀበው፤ በዚህ ቀን ሙሉ እረፍት ስለሚገባት ነው ብላ አስረድታታለች።

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ምሁራንን ባነጋገረችበት ወቅት ሴቶች በወር አበባ ጊዜያቸው ቤተ-መቅደስ ምክንያት ማስረጃዎች የሚፃረሩ ሆነው ነበር ያገኘችው።

አንደኛው ቻውፓዲ የተሰኘውን የሒንዱ ባህል በመጥቀስ ሴቶች በወር አበባቸው ንፅህና የተጓደላቸውና ዕድለቢስ መሆናቸውን አስረዳት። አንድ ቄስ ደግሞ በወር አበባቸው ጊዜ ሴቶች በጣም ንፁህ በመሆናቸው በሌሎች ሊቆሽሹ እንደሚችሉ አስረድቷታል።


ዶ/ር አርቪንድ ሻርማ በሞንትሬያል መጊል ዩኒቨርሲቲ የሐይማኖት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፤ እሳቸውም የሴቶችን ድርሻ በሒንዱዝም ውስጥ ነው በቅርብ ያጠኑት። እሳቸውም ይህ በባህላዊ አከባበር ወቅት ባለ ንፅህና ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

'' ሰዎች ለባህላዊ አከባበር ንፁህ ወይም ብቁ የማይሆኑባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ከሬሳ ወይም ከአይነ-ምድር ጋር ከተነካኩ። ሴቶችም በወር አበባቸው ወቅት እንደዚያው ነው የሚቆጠሩት'' ብለዋል።

''የሃይማኖቱ መጻሕፍት ይህን ማስረጃ ለምን እንደማያስቀምጡ ማስራዳት ይከብዳል'' ብለው በመቀጠል '' ይህን የሒንዱዝም ሥርዓት የሚከተሉት ስማርታ ሒንዱዊም የተባሉት ናቸው። እነሱም በጥንት የስሚርቲስ የሒንዱ መጻሕፍት ላይ የሚገኙ ናቸው። በሻክታ ሒንዱዊዝም ግን የወር አበባ የሚያነፃ እንጂ እንደሚያቆሽሽ ተደርጎ አይታመንም'' ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ አንስቶ ስለወር አበባ በጣም እየተወራ ነው። ለምሳሌ በክፍለ ሃገራት ላሉ ሴቶች የወር አበባ መጠበቂያ የመስጠት እቅዶችም ወጥተዋል።

በሕንድ ሴቶች የማህበራዊ ድረ-ገጾችን በመጠቀም ''ሃፒ ቱ ብሊድ'' ወይም 'በመድማቴ ደስተኛ ነኝ' የሚሉ ሃሽታጎችን በመጠቀም በወር አበባ ዙሪያ ያለውን ነውር እየተገዳደሩ ይገኛሉ።

'ፓድ ማን' የተሰኘው የቅርብ ጊዜ የቦሊዉድም ፊልም የዓለማችን የመጀመሪያው የወር አበባ ፊልም በመባል ተሰይሟል።

Image copyright Vidya Nair
አጭር የምስል መግለጫ የራሜስዋራም ባለ 1000 አምድ መተላለፊያ

ፊልሙ በአሩናቻላም ሙሩጋናንታም ሕይወት የሚያጠነጥን ሲሆን እሷም በታሚል ናዱ የምትገኝ አክቲቪስት ስትሆን በተለያዩ ክፍለ ሃገራት ላሉ ሴቶች በርካሽ የወር አበባ መጠበቂያ እንዲያገኙ የተሟገተች ናት።

ዋናው ተዋናይ አክሻይ ኩማር እንዲህ ብሏል ''ሕይወቴን በሙሉ ከሴቶች ጋር ነው የኖርኩት። ሆኖም ግን ይህንን ፊልም ስሠራ በጣም ብዙ ነው የተማርኩት። ያለነው በድንጋይ ዘመን አይደልም የወር አበባ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው።''

ሜጋ ቤተሰቧ ከቤተ-መቅደስ እስኪወጣ ድረስ ይህን ሁሉ በጭንቅላቷ ስታጠነጥን ነበር።

ለመጨረሻው ሥነ-ሥርዓት መምጣት ያልቻለችውን ዘመዷን ለማነጋገር ስልኳን ከቦርሳዋ አወጣች። እሷም አዘነችላት።

በመጨረሻም "የወር አበባሽ ላይ እንደነበርሽ መናገር አልነበረብሽም። አያውቁም ነበር'' በማለት ጻፈችላት።

ሜጋ ''አንቺ በወር አበባሽ ጊዜ ቤተ-መቅደስ ገብተሽ ታውቂያለሽ?'' ብላ ጠየቀቻት።

እሷም ቀስ ብላ ''በእኛ ዕድሜ ያሉ ሴቶች ይሄዳሉ። ማንም ካላወቀ ችግር የለውም'' ብላ ቀለል አድርጋ ነገረቻት።