የ2018ን ኦስካር ሽልማት ያገኘችውን ፍራንስስ ማክዶርማን ሽልማት የሰረቀው ግለሰብ በቁጥጥር ላይ ዋለ

ፍራንስስ ማክዶርማን የኦስካር ሽልማቷን ይዛ Image copyright AFP

እሁድ ዕለት ከተካሄደው የኦስካር ሽልማት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ፍራንስስ ማክዶርማንድ የተቀበለችውን ሽልማት የሰረቀው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ።

ሽልማቷ በሃገረ ገዢው ግብዣ ላይ መጥፋቱ እንደታወቀ ቴሪ ብራያንት በከባድ ስርቆት በቁጥጥር ስር እንደዋለ የሎስ አንጀለስ ፖሊስ አረጋግጧል።

የ47 ዓመቱ ቴሪ ከታሰረ በኋላ የ20 000 ዶላር ዋስ ጠርቶ እንዲለቀቅ ተወስኗል። ፍርድ ቤት የሚቀርብበትም ቀን እንዳልተቆረጠ ተገልጿል።

ሽልማቱም በምርጥ ተዋናይቷ እጅ ተመልሶ ገብቷል።

የተዋናይቷ ተወካይ ለዩኤስ ኤ ቱዴይ ''ፍራን እና ኦስካር በሰላም ተገናኝተው አብረው ኢን ኤን አውት በርግር እያጣጣሙ ነው'' ብላለች።

ፍራንስስ ሃውልቱ ከመሰረቁ በፊት ስሟን አስቀርፃበት ነበር።

ተዋናይቷ 'ትሪ ቢልቦርድስ አውትሳይድ ኤቢንግ ሚዙሪ' በተሰኘው ፊልም ላይ ለነበራት ሚና ባገኘችው የምርጥ ተዋናይነት ሽልማትን እያከበረች ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፍራንስስ በሃገረ ገዢው ዝግጅት ላይ ከመጥፋቱ በፊት ሃውልቷ ላይ ስሟን ስታስቀርጽ

ፍራንስስ ሽልማቱን ስትቀበል ባደረገችው ንግግር ላይ ሴት እጩዎችን በሙሉ አንዲቆሙ በመበጋበዟ የጋለ ተቀባይነት ነበር ያገኘችው።

ንግግሯንም ''የዛሬን ምሽት በሁለት ቃላት ነው የምስናበታችሁ - 'ኢንክሉዥን ራይደር' '' ብላ ነበር።

ኢንክሉዥን ራይደር ማለት ተዋናዮች ውላቸው ላይ ቢያንስ 50% ብዝሃነት ከተዋናዮች አንፃር ብቻ ሳይሆን ከፊልሙ ጀርባ ያሉትንም ጨምሮ እንዲካተት የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ማስተወሷ እንደነበር ከመድረክ ከወረደች በኋላ አስረድታለች።

ፍራንስስን ለኦስካር ሽልማት ባበቃት ፊልም ላይ የተወነችው ልጇ ተደፍራ ከተገደለችባት በኋላ ባለሥልጣናት ምንም ስላላደረጉላት ለመበቀል የተነሳችን እናት ወክላ ነው።

ተዋናይቷ ይህ ሁለተኛ የኦስካር ሽልማት ሲሆን የመጀመሪያ ኦስካሯን ያገኘችው ከ21 አመት በፊት 'ፋርጎ' በተሰኘ ፊልሟ ነው።