ኤርትራውያን ስደተኞች በእስራኤል በገደብ እንዲንቀሳቀሱ ተፈቀደላቸው

ኤርትራውያን ስደተኞች Image copyright Getty Images

በእስራኤል በስደተኞች ማቆያ ስፍራ የሚገኙ ኤርትራውያን ከማቆያ ስፍራው መውጣት የሚያስችል የአንድ ወይንም የሁለት ወር ፈቃድ እንደተሰጣቸው ለቢቢሲ ተናገሩ። ሆኖም ግን የሚፈልጉት ቦታ መሄድ እንደማይችሉ ጨምረው ገልፀዋል።

እንደ ስደተኞቹ ገለፃ ከሆነ የእስራኤል ሰባት ዋና ዋና ከተማዎች መግባት አይችሉም።

ኤርትራውያኖቹ ይህ ውሳኔ እነሱን የመከፋፈል ዓለማ የያዘና ሥራ ማግኘት አቅቷቸው ሃገር ለቀው እንዲወጡ ማሰገደጃ መንገድ ነው ብለው ይሰጋሉ።

በደቡብ እስራኤል ባለው በሆሎት የስደተኞች የማቆያ ስፈራ የሚገኙ 500 ኤርትራውያን ዕጣ ፈንታቸው እስከ አሁን ድረስ አይታወቅም።

የእስራኤል መንግሥት ደግሞ እነሱንም ጨምሮ ሌሎች ጥገኝነት የጠየቁ 30 000 አፍሪካውያን ሃገር ለቀው እንዲወጡ ይፈልጋል።

እስራኤል ስደተኞቹ ወደየሃገራቸው ወይም ደግሞ ወደ ሦስተኛ የአፍሪካ ሃገር እንዲሄዱ የ60 ቀናት ጊዜ ገደብ ሰጥታ እንደነበር ይታወሳል።

እስራኤልን ለቆ መሄድ የማይፈልግ ማንኛውም ግለሰብ እስራት የሚጠብቀው ቢሆንም ሴቶች፣ ልጆችና ቤተሰብ ያላቸው ወንዶች ግን ለተገደበ ጊዜ መቆየት እንደሚችሉ አሳውቀዋል።

ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ከእስራኤል ስደተኞቹን ለመቀበል ከተስማሙት ሃገራት መካከል ናቸውቢባልም ሀገራቱ ግን ይህንን ውንጀላ አይቀበሉትም።

ሁለቱም ሃገራት ስደተኞቹን ለመቀበል የ3.5 ሺህ ዶላር ክፍያ ሊቀበሉ ይችላሉ ተብሏል።

የኤርትራ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራውያን ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው እንደሚለሱ የሚፈቀድላቸው ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ዶላር የሚሰጣቸው ብቻ ከሆነ ነው ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ