አባቶች ወደ ሴት ልጆቻቸው የዘር ከረጢት ካንሰር የማስተላለፍ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው

አባት እና ሴት ልጁ Image copyright Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ሳይንቲስቶች የዘር ከረጢት ካንሰር የሚያመጣ ከአባት ወደ ሴት ልጅ የሚተላለፍ አዲስ የጅን መለወጥ ሂደት መኖሩን አረጋገጡ።

ይህ 'ኤክስ ክሮሞዞም' ከሚባለው የሚመጣ ሲሆን በተለምዶ ሴቶች በሚያደርጓቸው ምርመራዎች የማይገኝ ነው።

ባለሙያዎች የጅኑን ሥራ ለማወቅ ብዙ ጥናት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የቅርብ ጊዜ ግኝቶች 'ፒሎስ ጌኔቲክስ' የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ይገኛሉ። PLoS Genetics

የቤተሰብ ችግር

በአሁን ወቅት በቤተሰባቸው የካንሰር ሕመምተኞች የነበሩ ሴቶች ካሉ ቢ ሲ አር ኤ የሚባለውን የጅን ምርመራ እንዲያደርጉ የሚደረግ ሲሆን ፣ ይህ ጅን በጡትና በዘር ከረጢት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸውን ከፍ የሚያደርግ ነው።

አንጀሊና ጆሊ የተሰኘችው ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ከእናቷ ቢአርሲኤ 1 የተሰኘውን ጅን በመውሰዷ ዶክተሮች በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድሏ 87 እንዲሁም በዘር ከረጢት የመያዝ ዕድሏ ደግሞ 50 በመቶ መሆኑን ሲነግሯት የመከላከያ ቀዶ ሕክምና አድርጋ ነበር።

ነገር ግን ተመራማሪዎች ያልታሰቡ የዘር ከረጢት ካንሰሮች በ ኤክስ ክሮሞዞም የሚተላለፉ በመሆናቸው ሴት ልጆች ከአባታቸው የሚወርሱት መሆኑን አሳውቀዋል።

Image copyright AFP/getty
አጭር የምስል መግለጫ አንጀሊና ጆሊ የመጀመሪያ መከላከያ ቀዶ ሕክምና ያደረገች አ.አ.አ በ2013 ነበር

ወንዶች አንድ ኤክስ ክሮሞዞም ወደ ሴት ልጃቸው ያስተላልፋሉ።

ዶ/ር ኬቪን ኤንግ እና የሮዝዌል ፓርክ የካንሰር ኢንስቲትዩት የሥራ ባልደረቦቹ በአባቶች ኤክስ ክሮሞዞም ላይ ያገኙትንና የጠረጠሩት ጅንን ለይተው በማጥናት ኤም ኤጂ ኢሲ 3 ብለው ሰይመውታል።

የዘር ከረጢት ካንሰር በእናት ጅን ከመተላለፍ ይልቅ ከአባት እና በአባት እናት ዘር በሚወረስ ጅን የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው ይላሉ። በተጨማሪም ይህ ጅን ከአባት ወደ ወንድ ልጅ የወንድ ዘር ካንሰር እንደሚያስተላልፍ ደርሰውበታል።

በኒው ዮርክ ባፋሎ በሚገኘው ሮዝዌል ፓርክ የተሟላ የካንሰር ሕክምና ማዕከል የተደረገው ጥናት መሪ ኬቪን ኤንግ ''ቀጥለን ማድረግ የሚጠበቅብን ትክክለኛውን ጅን ማግኘታችንን ማረጋገጥ ነው። በመሥሪያ ቤታችን ይህ ግኝት ብዙ ውይይቶችን አስከትሏል፤ ምክንያቱም የተያያዙትን ኤክስ ክሮሞዞምን ቤተሰብ ማግኘት ያስፈልጋል'' ብለዋል።

''ሦስት ሴት ልጆች ያሉበትን ቤተሰብ ብንወስድ የዘር ከረጢት ካንሰር ሊያጠቃ የሚችለው ከቢ አር ሲ ኤ ጅን ይልቅ የኤክስ ክሮሞዞም መለዋወጥ ያለባቸውን ነው'' በማለት ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ምርምር ማእከል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ካትሪም ፒክወርት ''ይህ ጥናት አንዳንድ ሴቶች በዘር ከረጢት ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው ከአባታቸው የሚመጣ ሲሆን በእናትም ሊተላለፍ ይችላል።'' ብለዋል።

''ይህ ምርምር ወደፊት ይህ የዘር ከረጢት ካንሰር በቤተሰባቸው ያለባቸውን ሴቶች ሊረዳ ይችላል። ምክንያቱም የበሽታውን እድገትና ለውጥ በቅርብ መከታተል ይቻላል።የዘር ከረጢት ካንሰር ብዙ ጊዜ የሚታየው በጣም ካደገና ለማዳን ከባድ ከሆነ በኋላ ነው። አሁን ግን ብዙ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል በተለይ ችግር ያለበትን ለይቶ አጥንቶ እንዴት የዘር ከረጢት ካንሰር እንደሚያስከትል ማወቅ ይገባል።''

አንዌን ጆንስ፥ ታርጌት ኦቫሪያን ካንሰር በተሰኘው ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲሆኑ '' እነዚህ ግኝቶች በተጨማሪ ጥናትና ምርምር መረጋገጥ አለባቸው። ይህም የዘር ከረጢት ካንሰርን የማሰወገድ ሥራው ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ ከማድረጉም ባሻገር በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶችን ሕይወት ሊያድን ይችላል'' ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች