በማንቼስር የምትኖረው ደራሲ ሕይወት የሚቀይር የ165 ሺህ ዶላር ሽልማት አገኘች

ጄኒፈር ናንሳቡጋ ማኩምቢ Image copyright Mark Rusher
አጭር የምስል መግለጫ ጄኒፈር ናንሳቡጋ ማኩምቢ ከኡጋንዳ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የመጣችው በ34 ዓመቷ ነበር

መኖሪያዋን ማንችስተር ያደረገችው እና ልብወለድ ሥራዋ በእንግሊዝ አታሚዎች ውድቅ የተደረገባት ጄኔፈር በዓለም ከፍተኛ የሆነውን የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ሽልማት አሸነፈች።

የጄኒፈር ናንሱቡጋ ማኩምቢ የተወለደችው ኡጋንዳ ሲሆን ወደ እንግሊዝ የዛሬ 17 ዓመት ነው የሄደችው። እሷም በዩናይትድ ስቴትስ ዬል ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን ዊንድሃም ካምቤል ሽልማት አሸንፋለች።

165 ሺህ ዶላር የሚሰጣት ጄኒፈር ''ለረዥም ጊዜ ገቢ እያገኘሁ አልነበረም'' ትላለች።

''ያለኝን በሙሉ ያዋልኩት ለጽሑፌ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር ለማመን ያቅታል'' ብላለች።

የሽልማቱ ገንዘብ ቡከር ፕራይዝ ከተሰኘው ታዋቂ ሽልማት ሁለት እጥፍ ይሆናል። አዘጋጆችም ለሥነ-ጽሑፍ ከተመደቡ ሽልማቶች በሙሉ፣ ከኖቤል ፕራይዝ ቀጥሎ ትልቁ ነው ይላሉ።

የእዚህ ዓመት ዊንድሃም ካምቤል ፕራይዝ በልቦለድ፣ በኢልቦለድ ፣ በድራማና በግጥም ያወዳደረ ሲሆን ማኩምቢ ከስምንት አሸናፊዎች መካከል አንዷ መሆን የቻለች ሲሆን አንድ የታተመ መጽሐፍ ብቻ ያላት ደራሲ ናት።

ሽልማቱን ከተቀበሉት መካከል ሣራ ቤክዌል እና ኦሊቭያ የሚሰኙ የእንግሊዝ ደራሲዎችም ይገኙበታል።

'አፍሪካዊነቱ የበዛበት'

ሽልማቱን የጀመሩት ዶናልድ ዊንድሃምና ሳንዲ ካምቤል የሚበሉ ግለሰቦች ናቸው።

ሽልማቱም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው እ.አ.አ በ2013 ''ደራሲዎች ስለ ገንዘብ ሳይጨነቁ በሥራቸው ላይ ሙሉ በሙሉ ማተኮር እንዲችሉ ታስቦ ነው።''

ማኩምቢ '' ሽልማቱ የአሜሪካ ነው። ደግሞም ከዚህ ቀደም ይህ ሽልማትን የሚያገኙ ደራሲዎች ብዙ መጽሐፍት ያሳተሙ ናቸው፤ ስለዚህ ከእነሱ መካከል አንዷ በመሆኔ በጣም ተገርምያለሁ'' ብላለች።

'ኪንቱ' የተሰኘው የማኩምቢ የመጀመሪያ መጽሐፍ ሲበዛ አፍሪካዊ ነው ተብሎ በእንግሊዝ ሃገር ተቀባይነት አጥቶ በኬንያ ውስጥ ከታተመ አራት ዓመታት ሆኖታል። ባለፈው ጥር ወር ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም ተለቋል።

Image copyright Oneworld Publications

ደራሲዋም የእንግሊዝ አታሚዎችና አንባብያን ስለ አፍሪካ የሚያውቁትንና የሚመስላቸውን ነው ማንበብ የሚፈልጉት ብላለች።

ኪንቱ ደግሞ ''እውነተኛ፣ ትክክለኛ አፍሪካ'' ነው በማለት ተናግራለች።

መጽሐፉ ሚት እና አፈ ታሪኮችን የያዘ ሲሆን በኡጋንዳ ለ250 ዓመታት ተጠንቁሎብናል ብሎ የሚያስብ የአንድን ቤተሰብ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ነው።

''አውሮፓን ሙሉ በሙሉ አውጥቺያታለሁ፤ ትንሽ የበዛባቸውም ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የተጠቀመኩት ቋንቋና የጻፍኩበት መንገድ እንግሊዞች ከለመዱት ወጣ ያለ ነው። አሁን ግን አዕምሮአቸውን እየከፈቱ ይመስለኛል'' ትላለች ጄኒፈር።

በመቀጠልም ''አንባብያን አሁን አሁን እየታወቃቸው መጥቷል። ምክንያቱም አፍሪካን መጎብኘት ከፈለግኩኝ ከአንድ አፍሪካዊ ዕይታ ቢነገር ያሻለኛል፤ ማወቅ የምትፈልገው ይህ ነው ተብሎ ከሚነገረኝ'' ብላለች።

አስገራሚው የእንግሊዝ ኑሮ

በመጪው ጥር የሚወጣውን የሚቀጥለውን መጽሐፏን ለመጻፍ ግን ብዙም ርቃ መጓዝ አልተጠበቀባትም። የመጽሐፉ ርዕስ 'ላቭ ሜድ ኢን ማንቼስተር' ማለትም በማንቼስተር የተሠራ ፍቅር የሚል ነው።

''ይህን ታሪክ የጻፍኩት ኡጋንዳ ላሉት ነው። እኛን እዚህ የሚያጋጥሙንን ነገሮች እንዲያውቁት ለማድረግ ነው'' ትላለች ጄኒፈር። ''መምጣት ትፈልጋላችሁ? አንዴ ቆዩ መጀመሪያ የኔን ታሪክ አንብቡት እያልኳቸው ነው።'' ብላለች።

መጽሐፏን የሚያነቡት የኡጋንዳ ነዋሪዎች ምን ያገኙበታል ታድያ?

''የተወራላቸው ዓለም አይደለም። ኡጋንዳ ስንሆን እንግሊዝ ሃገር የለንደን ዓይን፣ በርክሂንገሃም ፓላስ፣ ሳቮይ እና ሪትዝ የተሰኙት ሆቴሎች ናቸው ምክንያቱም እንግሊዝ እራሷን እንዲህ ነው የምትሸጠው'' በማለት ተናግራለች።

''የሠራተኛውን መደብ መቼም አናየውም። ይህም ነው ደግሞ ሳይታሰብ የሚይዘው፣ ያስደነግጣል'' ብላለች።

ቀጥላም ''እዚህ መጥተን ደግሞ የሠራተኛውን መደብ ስናይ .. ወይ ጉድ ዲከንስን በደንብ መከታተል ነበረብኝ ያስብላል'' በማለት ተናግራለች።

ተያያዥ ርዕሶች