የሶማሊያ ፓርላማ ኢትዮጵያ ባለድርሻ የሆነችበትን የወደብ ስምምነት ተቃወመ

የበርበራ ወደብ በከፊል Image copyright JAMES JEFFREY

የእራሷን ነፃነት ያወጀችው ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ ባለድረሻ የሆነችበትን ከዩናይትድ አረብ ኤምሬት ኩባንያ ጋር የበርበራ ወደብን ለማስተዳደር የደረሰችውን አወዛጋቢ ስምምነት የሶማሊያ የፓርላማ አባላት ውድቅ አደረጉት።

የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ባለስልጣናት በቅርቡ ከዱባዩ ኩባንያ ዲፒ ዎርልድ ጋር የበርበራ ወደብን በጋራ ለማስተዳደር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ወደብ አላባዋ ጎረቤት ኢትዮጵያም ከኩባንያው በተጨማሪ የስምምነቱ አካል ናት። ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ መያዟን ወደቡን ለማስተዳድር ከፍተኛውን ድረሻ የወሰደው የዱባዩ ኩባንያ መግለፁ ይታወሳል።

ከስምምነቱ በኋላ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ኩባንያው 51 በመቶ፣ የሶማሌላንድ መንግሥት 30 በመቶ እና ቀሪውን 19 በመቶ ወደቡን የማስተዳደር ድርሻ ኢትዮጵያ እንደሚይዙ ተዘግቧል።

በስምምንቱ መሰረት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለገቢ እና ወጪ ንግዷ ለመጠቀም የሚያስችላትን መሰረተ ልማት እንደምታለማ ተገልፆ ነበር።

የዚህ ስምምነት ይፋ መሆንን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ለአረብ ሊግ ባቀረበው ጥያቄ፤ ስምምነቱ የሃገሪቱን አንድነትና ሕገ-መንግሥትን የሚፃረር በመሆኑ ውድቅ እንዲያደርገው ጥያቄ አቅርባለች።

ሶማሊላንድ እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ እነደ ሃገር እውቅናን ያላገኘች ሲሆን፤ ይህ ወደብን የተመለከተው ስምምነት ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበተጠ ያሻግረዋል ተብሎ ተሰግቷል።

ባለፈው ዓመት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመን የሚገኙትን የሁቲ አማፅያንን ለመውጋት እንዲያስችላት በበርበራ ወደብ ላይ ጦር ሰፈር እንድታቋቁም የሶማሊላንድ የፓርላማ አባላት መስማማታቸው ይታወሳል።