ጠ/ሚ ሜይ ሞስኮ በሰላዩ መመረዝ ጉዳይ አስተያየት መስጠት አለባት ብለዋል

ቴሬዛ ሜይ የሕዝብ ተወካዮችን ሲያነጋግሩ
አጭር የምስል መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ጋር ካደረጉት ስብሰባ በኃላ ሕዝብ ተወካዮችን አነጋግረዋል

የቀድሞው የሩሲያ ሰላይ እና ልጁን ለመመረዝ ጥቅም ላይ የዋለው ኬሚካል ነርቭን የሚያሽመደምድና በሩስያ ወታደራዊ ኃይል የተሠራ ነው በማለት ቴሬዛ ሜይ ለእንግሊዝ ሕዝብ ተወካዮች ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በሳልዝበሪ የተደረገው ጥቃት የሩስያ እጅ የሚኖርበት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል። የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሩስያውን አምባሰደር በመጥራት ሁኔታውን እንዲያስረዱ ጠይቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ እስከ ማክሰኞ ባለው ጊዜ ውስጥ አጥጋቢ መልስ ካልተሰጠ ሞስኮ ሕጋዊ ያልሆነ ኃይል ተጠቅማለች ብላ ዩናይትድ ኪንግደም እንድትደመድም ትገደዳለችም ብለዋል።

ጥቃቱን ለማድረስ የተጠቀሙበት ኬሚካል 'ኖቪቾክ' በመባል የሚታወቀው መርዝ መሆኑ እንደተደረሰበትም ጠቅላይ ሚንስትሯ ተናግረዋል።

ቴሬዛ ''ይህ ሩስያ በቀጥታ በሃገራችን ላይ የወሰደችው እርምጃ እንደሆነ ወይም ደግሞ የሩስያ መንግሥት አደገኛና ነርቭ ጎጂ የሆነው መርዝ ቁጥጥሩን አጥቶ በሌላ ሰው እጅ እንደገባ ያሳያል'' ብለዋል።

የእንግሊዙ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለሩስያ አምባሳደር እንደተናገሩት ሞስኮ ኖቪቾክ የተሰኘውን ነርቭ ጎጂ ኬሚካል ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ለዓለም አቀፉ የኬሚካል መሣሪያዎች እገዳ ድርጅት ማስረከብ አለባት።

Image copyright EPA/ Yulia Skripal/Facebook
አጭር የምስል መግለጫ የ66 ዓመቱ የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ እና ልጁ

ቴሬዛ አክለውም ዩናይትድ ኪንግደም ወደፊት ከባድ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት እንደሚያስፈልጋትና ከሩስያ ምንም ምላሽ ካልመጣ በረቡዕ ዕለት እርምጃዎቹን እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።

ባላፈው ሳምንት እሁድ ጡረተኛው የሩስያ ወታደር የ66 ዓመቱ ሰርጌ ስክሪፓል እና የ33 ዓመት ልጁ ዩሊ ስክሪፓል በሳልዝበሪ የገበያ ማዕከል በአግዳሚ ወንበር ላይ ነበር እራሳቸውን ስተው የተገኙት። እስካሁን ጤናቸው አስጊ ደረጃ ላይ ቢደርስም ግን በሕይወት እንዳሉ ተነግሯል።

ሰርጌ በአውሮፓውያኑ 2004 ለኤምአይሲክስ ምስጢር አቀብለሃል ተብሎ በሩስያ መንግሥት ከተከሰሰ በኋላ በ2010 የሰላዮች ልውውጥ ሲደረግ በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ተስጥቶት ነበር።

ኖቮቾክ ምንድን ነው?

  • በሩስያኛ 'አዲስ መጪ' ማለት ሲሆን እ.አ.አ በ1970ና በ1980ዎቹ በሶቭየት ሕብረት የተሠራ በነርቭ ላይ ጉዳት የሚያመጣ ኬሚካል ነው።
  • ኤ-230 የተሰኘው አንድ ኬሚካል ቪኤክስ ከሚባለው ነርቭን የሚጎዳ ኬሚካል አምስት ወይም ስምንት እጥፍ ጎጂ ሲሆን አንድን ሰው በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ሊጎዳ ይችላል።
  • በፈሳሽና ጠጣር መልክ እንደሚሰራ ይታመናል። አንዳንዶቹ ደግሞ ሁለትዮሽ መሣሪያ መሆናቸው ይነገራል። ይህ ማለት ደግሞ ለየብቻ ብዙም ጎጂ ያልሆኑ ሲሆን ሲቀላቀሉ ግን ሊገድሉ ይችላሉ።
  • አንደኛው የዚህ ኬሚካል ዓይነት በሩስያ ወታደራዊ ኃይል ለኬሚካል መሣሪያነቱ ፈቃድ አጝኝቷል።
  • በዓለም አቀፍ መርማሪዎች እንዳይገኝ ተደርጎ የተሠራው ይህ ኬሚካል ሊታወቅ የቻለው ከሩስያ በሸሹ ሰዎች ጥቆማ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ የሕዝብ ተወካዮችን ሲያነጋግሩ ''እንደዚህ ዓይነት ነርቭ ጎጂን መርዝ ተጠቅሞ ለመግደል የተደረገው ሙከራ በስክሪፓል ቤተሰብ ላይ ብቻ የተደረግ ጥቃት አይደለም'' ብለዋል። አክለውም "ይህ ዩናይትድ ኪንግደም ላይ የተሰነዘረ ጥንቃቄ የጎደለው ድርጊት የብዙ ንጹሃን ግለሰቦችን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ ነው'' ብለዋል።

ጣታቸውን ወደ ሩስያ ለመቀሰር ውሳኔ የወሰዱት ''ሩስያ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የመንግሥት እጅ ያለበት ግድያዎች በማካሄዷ እና ሃገር ሸሽተው የወጡ ሰዎች ለእንደዚህ ዓይነት ግድያዎች ዒላማ የተጋለጡ በመሆናቸው ነው'' ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የሌበር ፓርቲ መሪ የሆነው ጄሬሚ ኮርብን ነገሮች የተወሳሰቡ ሳይመጡ ከሩስያ ጋር ጠጣር ንግግር እንደሚያስፈልግ አሳውቀዋል።

Image copyright PA
አጭር የምስል መግለጫ መርማሪዎች በሳልዝበሪ አካባቢ የነበረን መኪና አስነሱ

ሰርከስ መሰል ሁኔታ

የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ጉዳይ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር እንደምትስማማ ተናግረዋል። ቴሬዛ ሜይ ሰኞ ዕለት ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግረው ነበር።

የኔቶ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ጄንስ ስቶለተንበርግ የነርቭ ጎጂው ኬሚካል አጠቃቀም ''አስቀያሚ እና ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል።

የሩስያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት ማሪያ ዛካሮቫ ቴሬዛ ሜይ ''በእንግሊዝ ፓርላማ ያደረጉት መግለጫ የሰርከስ ትርዒት ነበር'' ብለዋል።

የቢቢሲ ፖለቲካ አርታዒ ሎራ ኩዎንዝበርግ በቦሪስ ጆንሰንና በሩስያው አምባሳደር አሌክሳንደር ያኮቬንኮ መካከል የተደረገው ንግግር የተረጋጋና ቀጥተኛ ነበር ብላለች። ሁለቱ እጅ እንዳልተጨባበጡና ቦሪስ ጆንሰን የእንግሊዝን ሕዝብ 'ቁጣ' እንዳንፀባረቁ አርታኢዋ ፅፋለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ