"በምን ማስተማመኛ ነው የምንመለሰው" የሞያሌ ተፈናቃዮች

የሞያሌ ከተማ

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማው አባላት ተደንግጎ ስራ ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ በአንዳንድ ስፍራዎች አለመረጋጋቶች ተስተውለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ነበር የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ አስር ሰላማዊ ሰዎች ተገድለው በርካቶች የቆሰሉት። ከዚህ ክስተት በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት ሃገር ኬንያ መሸሽ ጀመሩ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም በበላይነት የሚቆጣጠረው ግብረ ኃይል ሴክሬታሪያት ተወካይ የሆኑት ሌተናል ጄኔራል ሃሰን ኢብራሂም በመንግሥታዊው ቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ አምስት የሠራዊቱ አባላት በደረሳቸው የተሳሳተ መረጃ ምክንያት ነው ተኩስ ከፍተው ዘጠኝ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎችን ሲገድሉ አስራ ሁለት ግለሰቦች ያቆሰሉት። አንድ ተጨማሪ ግለሰብ ሕይወቱ እንዳለፈ የተዘገበው ከተወካዩ መግለጫ በኋላ ነው።

የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች የሚገኙበት ቡድን ወደ ሥፍራው ማቅናቱን እና ጥቃቱን ያደረሱት የሠራዊቱ አባላት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ተደርገው ምርምራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተወካዩ ጨምረው ተናግረዋል።

ይህ ድርጊት ከተፈፀመ በኋላ ባለው ጊዜ ነው ታድያ የሞያሌ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሰል ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው በመስጋት ወደ ኬንያ መሰደድ የጀመሩት።

በክስተቱ አጎቱን ያጣ ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገ ግለሰብ ሁኔታውን ሲያስረዳን "ይጠብቀናል ብለን ያመንነው መንግሥት ነው እኛን የፈጀን" ይላል። "እና በዚህ ሁኔታ በምን ማስተማመኛ ነው የምንመለሰው" ይለናል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በርካታ ሰዎች ከሞያሌ በመሸሽ ወደ ኬንያ ገብተዋል

ድንበር ተሻግረው ኬንያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ የአማርኛው ክፍል እንደተናገሩት ቁጥራቸው የትየሌለ የሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም እየተሰደዱ ናቸው። የውጭ ጉዳይ እና የኬንያ ቀይ መስቀል ማሕበር ትብብር እያደረጉላቸው እንደሆነም ነው ተፈናቃዮቹ የነገሩን።

የከተማው የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ የሆኑ ግለሰብ እንደነገሩን ከተማዋ አሁንም እንቅስቃሴ አይታይባትም። የሞያሌ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ አስቻለው ዮሃንስ በበኩላቸው የተፈናቃዮቹ ቁጥር መጨመሩንና መንግሥት የተለያየ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቃሰ እንደሆነ ነው የነገሩን።

"እስካሁን 50 ሺህ ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ እና ድንበር ተሻግረው ኬንያ እንደገቡ ነው መረጃው ያለኝ" የሚሉት ከንቲባው "ከፍተኛ ባልስልጣናት መጥተው አስፈላጊው እርዳታ እንዲደረግ ርብርብ ላይ ነን" ሲሉ ያክላሉ።

"እየተፈናቀሉ ያሉትን ጨምሮ ድንበር አቋርጠው የሄዱትን መልሶ እንዴት ማቋቋም ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ እየመከርን ነን" ባይም ናቸው ከንቲባው።

በኬንያ የመርሳቤት ካውንቲ የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ መሊቻ ቦሩ ከኢትዮጵያ ሞያሌ ተፈናቅለው ኬንያ የገቡ ሰዎች በአራት የተለያዩ መጠለያ ውስጥ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

"ትክክለኛውን የተፈናቃዮች ቁጥር ከቀይ መስቀል ማሕበር ለማግኘት እየጣርን ነው" የሚሉት አቶ መሊቻ "የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከካውንቲያችን አቅም በላይ ነው። ለተባበሩት መንግሥታትና ለቀይ መስቀል የትብብር መልዕክት ልከናል" ይላሉ።

አቶ መሊቻ ቦሩ አክለውም ዛሬ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ከአባገዳው ጋር በመሆን ወደ አካባቢው ቢመጡም የረባ ንግግር ሳያደርጉ መመለሳቸውን ገልፀዋል።

ትላንት ምሽቱን ባገኘነው መረጃ መሰረት የኬኒያ ቀይ መስቀል ማህበር 2000 ተፈናቃዮችን መቀበሉን ገልጿል።

በርካታ ሰዎች ከሞያሌ በመሸሽ ወደ ኬንያ ገብተዋል