ካለሁበት 24፡ ሃገርና ወገን ውበት ነው

ኦብሴ ሉቦ Image copyright Obse Luboo

ስሜ ኦብሴ ሉቦ ይባላል። በካሊፎረንያ ክፍለ ግዛት በብሬያ ከተማ ከባለቤቴና ከአንድ ልጄ ጋር ነው የምኖረው።

ወደ አሜሪካ የመጣሁት ከአስራ ስምንት ዓመት በፊት ሲሆን፤ አቋርጬ የመጣሁትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እዚህ በመቀጠልና ከፍተኛ ዉጤት በማምጣቴ ሙሉ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቼ የጤና ባለሙያ መሆን ችያለሁ።

ትምህርቴንም እንዳጠናቀቅኩኝ ከሚኒሶታ ወደ ካሊፎርኒያ ጥሩ ሥራ አግኝቼ ሄድኩ። እስከ አውሮፓውያኑ 2009 (እ.አ.አ) እዚህ ሥራ ላይ ከቆየሁ በኋላ በዚህ ሃገርና በሃገራችን መካከል ያለውን የጤና አገልግሎት ልዩነት እያሰብኩ እንዴት ወደ ሃገሬ ተመልሼ የአቅሜን ማበርከት እንደምችል ማውጠንጠን ጀመርኩኝ።

በተለይም እዚህ ሃገር የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱና በአዳዲስ የተተኩትን የህክምና መሣሪያዎች ወደ ሃገር ቤት ቢሄዱ ምን ያህል አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚችሉ ብዙ ጊዜ አስባለሁ። ከዚያም የነፃ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ተወለድኩበት ምዕራብ ወለጋ አካባቢ ወደ ነጆ ሆስፒታል ሄድኩኝ።

በአጭር ጊዜ ቆይታ በሕፃናት፣ በሴቶችና በአዋቂዎች ጤና አገልግሎት መጓደል የተነሳ የሚደርሰውን ስቃይና ሞትን በማየቴ በእጅጉ አዘንኩኝ።

Image copyright Obse Luboo

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በዙሪያዬ ያሉትን የተለያዩ ሰዎች በማስተባበር በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በልዩ ልዩ የሕክምና ሙያቸው ማገልገል የሚችሉትንም ጭምር በመጋበዝ ወደ ሃገር ቤት ይዤ ሄጄ የቻልኩትን መሥራት ጀመርኩኝ።

ከተሠሩት ሥራዎች መካከል በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ሕፃናትን በማከም እንዲሁም በሃገር ውስጥ ሊታከሙ የማይችሉትን ደግሞ ወደ ዉጪ ሃገር ወስዶ ማሳከም ጭምር ይገኝበታል።

በተጨማሪም ደግሞ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ለማየት የተቸገሩ ሰዎች የቀዶ ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ያስቻሉ የተለያዩ ዘመቻዎችን አድርገናል።

አሜሪካንን ልዩ የሚያደርጋት ትልቁ ነገር ነፃነትና ለሰብዓዊ መብት ያለው ክብር ነው። በተለይም የመናገር ነፃነት በመኖሩ ማንኛውም ሰው እራሱን ሲገልጽ የሚነካውም ሆነ የሚያሰጋው ምንም ነገር የለም። ይህን ነፃነት ደግሞ በጣም እወደዋለሁ።

በዚህ ሃገር ከሚገኙ ምግቦች ከባሕር የሚወጡ የዓሣ ዓይነቶችን በጣም እወዳለሁ።

የሃገሬ ሰውንም ሆነ ምድሯ እንዲሁም ብዙ ነገሮች በጣም ይናፍቁኛል። በተለይም እናትና አባቴን ከሁሉ በላይ ይናፍቁኛል። ሃገርና ወገን ውበት ነው። የአንድ ሃገር ሃብት እነዚህ ናቸው። ስለዚህም የሰዉና የእንስሳው ጤንነት መጠበቅ አለበት። ለመሬቱም ደህንነትና እንክብካቤ መደረግ አለበት ብዬ አምናለሁ።

በምኖርባት የብሬያ ከተማ አካባቢ ብዙ የሚያማምሩ የባሕር ዳርቻዎችና የመናፈሻ ሥፍራዎች አሉ። እኔ የምኖርበት አካባቢ ያለው ስቲንሰን ቢች የሚባለው ሲሆን አንዳንዴ ለመቆዘምም ሆነ ለመዝናናት እሄዳለሁ።

Image copyright Obsee Luboo

ሁሌም 'ጎልደን ጌት' የተሰኘውን ድልድይ እወደዋለሁም እደነቅበታለሁም። ይህ ድልድይ በጣም ትልቅ ሲሆን በጣም ታዋቂም ነው። የዚህ ሃገርም ሆነ ከሌላ ሃገር የሚመጡ ሰዎች የሚጎበኙት ነው። ባለፍኩ ባገደምኩ ቁጥር አሠራሩን፣ ትልቅነቱን፣ የፈጀውን የሰው ኃይል ጨምሮ ሳስብ እግዚያብሔር ለሰው የሰጠውን ጥበብን ስለሚያሳየኝ እደነቃለሁ።

እዚህ ከመጣሁ አንስቶ ካጋጠሙኝ ነገሮች ከሁሉም በላይ የሚያስደስተኝ ትምህርቴን ጥራት ባለው መልኩ በመጨረሴና በተማርኩትና ባካበትኩት ልምድ ደግሞ ሃገሬን መርዳት መቻሌ ነው። እንዲሁም ከተለያዩ ሃገራት ከተወጣጡ ሰዎችም ጋር በመተዋወቄ በሃገር ቤት የምሠራቸው ሥራዎችም ላይ ማሳተፍ በመቻሌ በጣም እደሰታለሁ።

ከምመኛቸው ነገሮች መካከል ደግሞ ለየት ያለ ኃይል ወይንም ሥልጣን ቢኖረኝ፤ የጤና ዘርፍ መርሃ ግብር መቀየር እፈልጋለሁ። እዚህም እንደኛው ሃገር ችግር አለ። በምኖርበት ከተማ ብዙ ሰዎች የጤና ችግር እያለባቸው መታከም የማይችሉበት ሁኔታ አለ።

Image copyright Obsee Luboo

ይህም የጤና አገልግሎቱ ወድ ከመሆኑ የተነሳ በሰዎቹ የኑሮ አቅም ላይ መሠረት ያደረገ ነው። ስለዚህ በማንኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች፤ ደሃም ሆነ ሃብታም፣ የመኖሪያ ፈቃድ ያለውም ሆነ የሌለው ሁሉ እኩል የሆነ የጤና አገልግሎት እንዲኖረው እመኛለሁ። በተለይም ለሕፃናት፣ ለሴቶችና ለአረጋዊያን ይህንን ማዳረስ ብችል ደስ ይለኛል።

በምኖርበት በብሬያ አካባቢ ብዙ ደኖች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የተለያዩ ዛፎች ይገኙባቸዋል። በተለይ ሃገሬን እንድናፍቅ ያደረገኝ አንድ ቀን ነጭ የባሕር ዛፍ ማየቴ ነበር። ወላጆቼ ልጅ እያለን ጉንፋን ሲይዘን ነጭ ባህር ዛፍ ያጥኑን ነበር። ባየሁት ቁጥር ደግሞ በሃሳብ ወደ ሃገሬ ይወስደኛል። በተለይ ከነጆ ወደ ጃርሶ ያለውን መንገድ ያስታውሰኛል።

እዚህ ሃገር ስመጣ ቋንቋ በደንብ አለመቻሌና ቤተሰቤን መናፈቄ ቶሎ መልመድ እንዳልችል አድርጎኝ ነበር። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ እንግሊዝኛን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንማራለን ነገር ግን መናገር ችግር ነው። ስለዚህ ለተወሰነ ጊዜ የቋንቋ እጥረት እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር።

ካለሁበት በቅፅበት ሃገሬ ወስዶ የሚጥለኝ ነገር ቢኖር እራሴን በተወለድኩበት ከተማ በቤተሰቦቼ ግቢ ውስጥ ማግኘት እፈልጋለሁ።

ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረችው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 25 ፡''የሰፈሬን አየር ድጋሚ ማጣጣም እፈልጋለሁ''

ካለሁበት 26 ፡ 'እዚህ አራስ፣ መታረስና ማረስ ብሎ ነገር አያውቁም'

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ