የእስራኤል ፍርድ ቤት ከአፍሪካ የሚመጡ ስደተኞችን የማባረር ዕቅድን ለጊዜው እንዲቋረጥ ወሰነ

አፍሪካዊ ስደተኞች ብዙዎቹ ከኤርትራ የመጡ በእየሩሳሌም ተቃውሞ እያካሄዱ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በእስራኤል በርካታ ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞች አሉ

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት ያወጣውን በሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካዊ ስደተኞችን የማባረር አወዛጋቢ ሕግ ለጊዜው እንዲቋረጥ ውሳኔ አስተላልፏል።

መንግሥት ዕቅዱን በዝርዝር እንዲያብራራም ፍርድ ቤቱ እስከ መጋቢት 17፣2010 ድረስ ቀነ-ገደብ ስጥቷል።

ባለፈው ጥር ወር በብዛት ከኤርትራና ከሱዳን የተወጣጡ ስደተኞች እስከ 3500 ዶላር እና የአውሮፕላን ጉዞ ቲኬት ተሰጥቷቸው በፈቃደኝነት እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ ወደ ሶስተኛ ሃገር እንዲሸጋገሩ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር።

ይህን ለመፈፀም ፍቃደኛ የማይሆኑ ስደተኞች በመጀመሪያ እስር ከዚያም ደግሞ ከሃገር መባረር እንደሚጠብቃቸው የእስራኤል ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ከኤርትራና ከሱዳን የተውጣጡ ስደተኞች የመንግሥትን ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰዱት በኃላ ነበር የእስራኤል ፍርድ ቤት ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው።

የእስራኤልም መንግሥት አሁን በፍርድ ቤቱ በተጠየቀው መሠረት ማብራሪያ እስከሚያቀርብ ድረስ ስደተኞቹን ከሃገር ማስወጣት አይችልም።

የእስራኤል ባለስልጣናት 'ድንበር ጣሾች' እያሉ የሚጠሯቸው ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ አፍሪካዊ ስደተኞች በእስራኤል ይኖራሉ።

ብዙዎቹ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ነበር በግብፅ በኩል ወደ እስራኤል የገቡት። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከግብጽን ከእስራኤል በሚያዋስነው በረሃማ ድንበር ላይ አጥር ተገንብቷል ይህም ወደ እስራኤል የሚደረገውን ሕገ-ወጥ ጉዞ በተወሰነ መልኩ እንዲቀንስ አስችሏል።

ይህ ስደተኖችን ከሀገር የማስወጣት ዕቅድ የሚመለከተው ያለገቡ ወንዶችን ብቻ ነው።

ሕፃናትን፣ ሴቶችን፣ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆች ወላጆችንና የባርነትና የሕገወጥ ሰዎች ዘውውር ተጠቂ የሆኑትን ሰዎች አይመለከትም።

ባለሥልጣኖች እንዳሉት ከሆነ የስደተኞቹ በሰብዓዊ መልኩና በፍላጎታቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ