ብላክቤሪ ስልኮች ለወንጀለኞች እየሰጡ ያሉት ጥቅም

Phantom Secure phones Image copyright Phantom Secure

ተንቀሳቃሽ ስማርት ስልኮችን በድብቅ በማምረት ለዓለማችን አደገኛ ወንጀሎች ያቀርባል ተብሎ የተወነጀለ የአንድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተቀማጭነቱን ካናዳ ያደረገው 'ፋንተም ሴክዩር' የተሰኘ ድርጅት ተሻሽለው የተሰሩ ብላክቤሪ ስልኮችን ለወንጀለኞች በመሸጥ በአስር ሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ አግበስብሷል ሲሉ መርማሪዎች እየወነጀሉት ይገኛሉ።

የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት ቪንሴንት ራሞስ የተሰኘውን ግለሰብና አጋሮቹን በሲያትል ከተማ በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።

ቢቢሲ ፋንተም ሴክዩር የተሰኘውን መሥሪያ ቤት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ከተያዙት ግለሰቦች መካከል ግን ቪንሴንት ራሞስ ብቻ በፖሊስ እጅ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ክሱ ደብቅ እና ሊጠለፉ የማይችሉ ስልኮችን ማምረትን ጨምሮ ዕፅ አዘዋወሪዎችን በመርዳት ወንጀል ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ወንጀለኛ ሆነው ከተገኙ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊፈርድባቸው ይችላል።

"ኩባንያው በመላው ዓለም ላሉ የዕፅ አዘዋዋሪወች አገልግሎት ሲሰጥ ነበር። ስልኮቹ የማይጠለፉ በመሆናቸው ከህግ ሰዎች ሊያመልጡም ችለዋል" ሲሉ የአሜሪካው ጠበቃ አዳም ብሬቭማን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌሎች ኩባንያዎች

ብላክቤሪ የተሰኘው የተንቀሳቃሽ ስልኮች አምራች ኩባንያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። መርማሪዎችም ኩባንያው በዚህ ህገ ወጥ ሂደት ውስጥ እጁ ይኑርበት አይኑርበት ማረጋገጣቸውን አልተናገሩም።

ጠበቃ ብሬቭማን እንደሚሉት ፋንተም ሴክዩር የተባለው ድርጅት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኩባንያዎችም በመሰል ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ። ምርመራችን በእነዚህ ተጠርጣሪ ድርጅቶችም ላይ ይቀጥላል ብለዋል።

ጠቃው አክለውም "ምንም እንኳ ሌሎች የተንቀሳቃሽ ስልክ አምራች ድርጅቶች የማይጠለፍ ስልክ ቢሰሩም ይህ ኩባንያ ግን የሚያመርታቸውን ስልኮች በጎ ላልሆነ አላማ እየተጠቀመባቸው መሆኑ ተጠያቂ ያደርገዋል" ይላሉ።

መርማሪዎች ማረጋገጥ እንደቻሉት ተጠቃሚዎችን እነዚህን ስልኩን ማግኘት የሚችሉት በጥቆማ እንጂ በቀጥታ አይደለም። ይህም የህግ ሰዎች የድርጅቱን ህገ-ወጥ ተግባር እንዳይደርሱበት ያደርጋል።

ፋንተም ሴክዩር ለደንበኞቹ አንድን ስልክ ከ2 ሺህ ዶላር እስከ 3 ሺህ ባለ ዋጋ ለስድስት ወራት ጥቅም ሲሸጥ ነበር።

መርማሪዎች እንደሚገምቱት ቢያንስ 20 ሺህ በፋንተም ሴክዩር ተሻሽለው የቀረቡ ስልኮች በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

በዚህ ስልክ በኩል የሚያደረጉ ግንኙነቶች ለመጠለፍም ሆነ ለመሰበር እጅጉን የሚያዳግቱ ሲሆን የዕሁፍ መልዕክቶችንም ተከታትሎ ለመጥለፍ የማይታሰብ ነው።

ምንም አንኳ የህግ ሰዎች መሰል መጠለፍ የማይችሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮች መብዘት ለወንጀለኞች ደብዛ መጥፋት አስተዋፅኦ እኣደረገ ነው ቢሉም የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ለሰዎች የግል ነፃነት መጠበቅ መሰል ስልኮች መኖራቸው አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ።