ለተማሪዎች የሚሰጠው የቤት ሥራ ምን ያህል ቢሆን ጥሩ ነው? ይህ ጥያቄ በወላጆችና በመምህራን ተደጋግሞ የሚጠየቅ ነው።

የቤት ሥራዎች ተማሪዎችን ለትምህርታቸው ያግዛሉ?

"አዎ" ይላል ላውረን "ምክንያቱም የቤት ሥራ ብለን የምንሠራውን ካወቅን፤ በሚቀጥለው ትምህርት ላይ ምን መሥራት እንዳለብን እንገነዘባለን።"

ግን የቤት ሥራ ይበዛል?

"አንዳንድ ጊዜ ይበዛል" ይላል ሪያን "የጥበብ ትምህርትን ለመሳሰሉ ትምህርቶች የሚሰጡት የቤት ሥራዎች ለወደፊቱ ብዙም የሚጠቅሙ አይመስሉኝም።"

የዘርፉ ባለሙያዎችስ ምን ይላሉ? ምላሻቸው የተደበላለቀ ነው።

ከአራት ዓመት በፊት ይፋ የሆነ አንድ ለትምህርት ሚኒስቴር የቀረበ ትልቅ ሪፖርት እንዳሰፈረው በሳምንቱ ቀናት በአማካይ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓታት የቤት ሥራ ለመሥራት የሚያጠፉ 9 ዓመት የሆናቸው ተማሪዎች የቤት ሥራ ከማይሠሩት ከአስር እጥፍ በላይ ጥሩ ውጤትን በፈተና ላይ ያስመዘግባሉ።

ታዲያ የቱ ጋር ነው መጠኑ የሚወሰነው? መቼ ነው የቤት ሥራ በጣም አስጨናቂ የሚሆነውና አሉታዊ ውጤትን የሚያስከትለው?

ይህም ሱተን በተባለው ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎች አብዝተው የሚያስቡት ጉዳይ ነው።

"የቤት ሥራው የሚበዛና በቶሎ ተሠርቶ መቅረብ ካለበት እንዲሁም ቤት ውስጥ የሚሠራ ሥራ ካለ በእርግጥም በጣም አስጨናቂ ነው'' ይላል ፖርሽ "አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ግን ጠቃሚ ይሆናል።"

"ሥራ ለማግኘት ሊረዳን ስለሚችል ሂሳብና የቋንቋ ትምህርትን በደንብ ማወቅ እንዳለብን በተደጋጋሚ ሲነገረን ቆይቷል" ትላለች ሳማንታ "አንዳንድ ጊዜ በጣም ቀላል ይሆናል፤ አዲስ ዓይነት የቤት ሥራ ከሆነ ግን ያስቸግራል።"

እስከ አውሮፓውያኑ 2012 ድረስ በእንግሊዝ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምን ያህል የቤት ሥራዎችን ለተማሪዎቻቸው መስጠት እንዳለባቸው ምክር ይሰጣቸው ነበር። ነገር ግን አሁን ለተማሪዎቻቸው በሚስማማ ሁኔታ እራሳቸው እንዲወስኑ ተደርጓል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ንፅፅሮች እንደሚያረጋግጡት አንድ ዓይነት ዘዴ ለሁሉም የትምህርት ስኬቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በቻይና የሚገኙ ተማሪዎች መጠኑ እጅግ የበዛ የቤት ሥራ የሚሰጣቸው ሲሆን በትምህርታቸውም ከፍተኛ ነጥብ ከሚያስመዘግቡ ተማሪዎች መካከልም ይመደባሉ።

ነገር ግን ጣሊያን ምንም እንኳን በአንፃራዊነት ከፍተኛ መጠን ያለው የቤት ሥራ ለተማሪዎቿ ብትሰጥም በውጤት ረገድ ግን የሚንፀባረቀው የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።

በተቃራኒው ፊንላንድ ውስጥ በእንግሊዝ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አንፃር ለቤት ሥራና ለፈተናዎች የሚሰጠው ትኩረት ዝቅ ያለ ነው።

ከብሔራዊ ትምህርት አንፃር ሌሎች ነገሮችም ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።

እያንዳንዳቸው ተማሪዎች የተለዩ በመሆኑ የሚሰጣቸውንም የሚሠሩት በተለያየ መንገድ ነው።

ትምህርት ቤቶችም የተለያዩ ደረጃዎች አሏቸው። በተጨማሪም ተማሪዎች በየቤታቸው ያላቸው የተረጋጋ ሕይወት በአጠቃላይ የትምህርት ተሳትፏቸውና የቤት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ብቃት ላይም ጉልህ ሚና አለው።

ለማጠቃለልም፤ የቤት ሥራ ጠቃሚ ነው በተማሪዎች ላይም ልዩነትን ያመጣል። ነገር ግን ቁጥሩ የበዛ የቤት ሥራ ለተማሪዎች መስጠት ጥሩ ውጤትን እንዲያመጡ አያደርጋቸውም።

በሌላ አባባል በቤት ሥራውና በዕለት ተለት ሕይወት ውስጥ ያለውን ሚዛን መጠበቅ በርካታ ወላጆችን የሚያሳስባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ በትምህርት ቤት ላሉ ተማሪዎችም ወሳኝ ነገር ነው።

ተያያዥ ርዕሶች