ካለሁበት 25 ፡''የሰፈሬን አየር ድጋሚ ማጣጣም እፈልጋለሁ''

ሚልኪያስ ሙሴ ዮሐንስ Image copyright Milkias M Yohannes

ስሜ ሚልኪያስ ሙሴ ዮሐንስ ይባላል። በሜሪላንድ ዋሽንግተን ዲሲ ነው የምኖረው።

የዛሬ 14 ዓመት ወደ አሜሪካ የገባሁት ስደተኛ ሆኜ ነበር።

ወደ አሜሪካ ከመግባቴ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል በሱዳን ቆይቼ ነበር።

ሃገሬ ውስጥ ምንም ብሩህ የሆነ የወደፊት ሕይወት ሊታየኝ ስላልቻለ ነበር ለመውጣት የወሰንኩት። ኤርትራን ትቼ እንድወጣ ያስገደደኝ ዋናው ምክንያት ደግሞ መጨረሻ በሌለው ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ምክንያት ነበር።

መጀመሪያ አሜሪካ ስገባ ከሃገሬ ጋር ያለው ልዩነት ወዲያው ነበር የታየኝ። በፍፁም እንደ ኤርትራ እንዳልሆነ ነበር የተገነዘብኩት።

የዚህን ሃገር ኑሮ ለመልመድ ጊዜ ቢፈጅም የግድ ግን ይለመዳል።

Image copyright Milkias M Yohannes

በአሜሪካ አንድ ዓመት ከቆየሁኝ በኋላ ትምህርቴን ለመቀጠል ወሰንኩኝ። በምኖርበት አካባቢ የምትገኝ አንዲት ኮሌጅ ነበረችና አዚያው ተመዝግቤ የሕክምና ትምህርቴን ቀጠልኩኝ።

ለአምስት ዓመታት ከተማርኩም በኋላ ተመረቅኩኝ።

አሁን የምሠራበት ደግሞ ለጡት ካንሰር ሕክምና የሚሆን መድሃኒት ለማግኘት ምርምር በሚያደርግ ድርጅት ውስጥ ነው። እዚያ ውስጥ ሙያዬ እየሠራሁ እገኛለሁ።

አሜሪካ ውስጥ ምንም አንኳን የሚፈለገው ምግብ ቢገኝም። እኔ ግን የምወደው የሃገራችንን እንጀራ ነው።

ያገኘሁትን አጋጣሚና ዕድል በመጠቀም ከጓደኞቼም ጋር ሆኜ ለብቻዬ ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ ምግብ ቤቶች በመሄድ እንጀራ እበላለሁ። እሱም በጣም ያስደስተኛል።

ሃገሬ ውስጥ የነበረኝ ማህበራዊ ኑሮ ሁሌም በጣም ይናፍቀኛል። ከተማ ውስጥ ከጓደኞቼ ጋር መንሸራሸር፣ ውጪ በነፃነት የምንጫወተውና አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ይናፍቃል።

ያደኩበትን ስፍራ ማሰቡና እዚያው ሄጄ ደግሞ መዝናናትን እንደ ትልቅ በረከት ነው የማየው።

Image copyright Alamy

አዚህ የምኖርበት ከተማ ውስጥ በጣም የሚገርመኝ፤ ሁሉም ሰው ሥራ ስለሚበዛበት እረፍት የሚባል ነገር የላቸውም ማለት እችላለሁ። ሰዎችን ስመለከት ሁልጊዜ እንደሮጡ ነው፤ ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ ይሮጣሉ።

ነገሮችን መቀየር አቅምና ችሎታ ቢኖረኝ፤ ይህንን የሩጫ ኑሮ ማሰቆምና ልክ እንደ ሃገራችን ሰዓቱ የሚታወቅ፣ ማህበራዊ ኑሮ ያለበትና የተረጋጋ ኑሮ እንዲጋባባቸው ማድረግ ብችል ድስ ይለኛል።

ከኤርትራ ወጥቼ ወደ ሱዳን በገባሁበት ጊዜ ሁሉም ነገር አዲስ ነበር የሆነብኝ። እዚያ ያገኘኋቸው ሰዎች ባህላቸው እኔ ከለመድኩትና ከማውቀው በጣም የተለየ ነበር።

ሰውን ከድንበር ወደ ድንበር ከሚያሸጋግሩት ሰዎች ጋር ደግሞ የግድ መስማማት ያስፈልግ ነበር።

ምክንያቱም ለገንዘብ ያላቸው ፍቅርና ስስት የተነሳ በመሃል ጉዞውን ያቋርጡ ነበር ። አንደዚህ ዓይነት ብዙ ችግሮች የገጠሙኝ ቢሆንም አንኳን አሁን ግን በአምላክ ብርታት አልፌዋለሁ፤ ረስቼዋለሁም።

የሚናፍቀኝ ነገር ቢኖር ያደኩበት ቦታ በቅፅበት ተመልሼ ደስ የሚለውን አየር እየተነፈስኩኝ ጎዳና ሃርነት በሚባለው ሰፈሬ ከጓደኞቼ ጋር ዘና ብዬ መጓዝ ብችል ደስ የለኛል ።

ለኤደን ሃብተሚካኤል እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 26 ፡ 'እዚህ አራስ፣ መታረስና ማረስ ብሎ ነገር አያውቁም'

ካለሁበት 27፡ 'እንጀራ ከበላሁ ዓመት አልፎኛል'

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ