እስራኤል የሶሪያን ኒውክሌር ማብላያ መምታቷን አመነች

እስራኤል በ2007 የአየር ጥቃት የደረሰበትን ኒውክሊዬር ማብላያ የሚያሳዩ ምስሎች ይፋ አደረገች Image copyright AFP/Getty Images

የእስራኤል ጦር ኃይል መዝገቦች ለመጀመሪያ ለሕዝብ ጊዜ ክፍት መደረጋቸውን ተከትሎ ሃገሪቱ በአውሮፓውያኑ 2007 ሶሪያ ውስጥ የሚገኝ የኒውክሌር መሣሪያ ማብላያ ማውደሟን ይፋ አድርጋለች።

በሶሪያ በስተምሥራቅ ባለ ዴይር አል ዙር በተሰኘ አካባቢ ላይ በሚገኝ የኒውክሌር ማብላያ ላይ ''ለእስራኤልም ሆነ ለአካባቢው ሃገራት አስጊ'' ሆኖ በመገኘቱ ነው የአየር ኃይል ጥቃት የተፈፀመው።

በተጨማሪም ማብላያው ሥራውን እያጠናቀቀ እንደነበር የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል አስታውቋል። ምንም እንኳ ጥቃቱን ያደረሰችወው እስራኤል እንደነበረች ቢታመንም ቴል-አቪቭ ጉዳዩን ስታስተባብል ነበር።

ሶሪያ በበኩሏ ጥቃት የደረሰበት አካባቢ የኒውክሊዬር ማብላያ አይደለም በማለት ስትክድ ቆይታለች።

እስራኤል ጥቃቱን ማድረሷን ለማመን የተገደደችው ስለጥቃቱ ማውራት ይከለክል የነበረው እገዳ በመነሳቱ ነው።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ አካባቢው ከድሮም የኒውክሊዬር ማብላያ መሆኑ ''አያጠራጥርም ነበር" ይላል። አክሎም ማብላያው የተገነባው በሰሜን ኮርያ እገዛ ሊሆን እንደሚችልም ድርጅቱ ይገምታል።

ሶሪያ 'ነን ፕሮሊፈሬሽን ትሪቲ' የተሰኘውና ኒውክሌር ማብላላ የሚያግደውን ስምምነት የተቀላቀለች ሲሆን ማብላያ የለኝም ብላ የካደችበት ዋነኛ ምክንያትም ይህ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።

Image copyright Getty Images

የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ምን ይላል?

ለሕዝብ ይፋ ከሆኑት ወታደራዊ መረጃዎች መካከል እስራኤል በሶሪያ አል ካቡር ላይ ያደረሰችውን ጥቃት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽና ቋሚ የፎቶ ፊልሞች ይገኛሉ።

''በአውሮፓውያኑ መስከረም 2007 የእስራኤል አየር ኃይል ሥራ ላይ የነበረውን የሶሪያን ኒውክሌር ማብላያ ጣብያ በምሽት መምታቷን ወታደራዊ ኃይሉ የሰጠው መግለጫ ያትታል።

እስራኤል '4 ኤፍ-ሲክስቲን' እና '4 ኤፍ-ፊፍቲን' የተሰኙ የጦር አውሮፕላኖችን በመጠቀም አካባቢውን ማፈንዳቷንም አሳውቀዋል።

በመግለጫው ላይ ''ጥቃቱን ያካሄድነው የእስራኤልን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ የእስራኤልን ህልውና ሊፈትኑ የሚችሉ በመሆናቸው ነው'' የሚል አንቀፅ ሰፍሯል።

የኢራን ወታደራዊ ኃይል ሶሪያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስራኤል ቀጣናውን በንቃት ከመጠበቅና ማስጠንቀቂያዎች ከመሰንዘር አልተቆጠበችም።