የንፁህ ውሃ ችግር ካለባቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት

ወረፋ ንፁህ ውሃ ለመቅዳት Image copyright AFP

የዓለም ውሃ ቀንን በማስመልከት የወጣ አዲስ ሪፖርት እንዳመለከተው ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማያገኙ ሰዎች ቁጥር ወደ 844 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ አመልክቷል።

ዋተር ኤይድ የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅትም የንፁህ ውሃ አቀርቦት ሳይኖር፤ ከጤና፣ ከትምህርትና ከፆታ እኩልነት ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ግቦችን ማሳካት ስለማይቻል ፖለቲከኞች ለውሃ አቅርቦት ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቀርቧል።

በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ዘጠኝ ሰዎች መካከል አንዱ የንፁህ ውሃ አቅርቦት የለውም። ዋተር ኤይድ የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት ይህንን እንዲል ያስቻለው፤ ሰዎች ምን ያህል ውሃን በቤታቸው ውስጥ ያገኛሉ ወይም ንፁህ ውሃን ለመቅዳት ከግማሽ ሰዓት በላይ በእግራቸው ለመጓዝ ይገደዳሉ የሚለውን በማጥናት ነው።

ንፁህ ውሃን የማያገኙ ሰዎችን ብዛትን በተመለከተ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ቻይናዊያንና ሕንዳዊያን ናቸው። ነገር ግን ሃገሮች ካላቸው የህዝብ ቁጥር አንፃር በመቶኛ ሲሰላ የውሃ ችግር በተለይ በአፍሪካ የከፋ ነው።

በንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግር በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ሃጋራትም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያና የዲሞክራቲክ ኮንጎ ናቸው።

ዋትር ኤይድ እንደሚለው 800 የሚደርሱ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ህፃናት ከንፁህ ውሃ እጦት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸውና ከተቅማጥ ጋር በተያያዙ ህመሞች በየዕለቱ ለሞት ይዳረጋሉ።

የወደፊቱን የዓለም የንፁህ ውሃ አቅርቦትን ከማረጋገጥ የበለጠ አሳሳቢ ጉዳይ ስለሌለ መሪዎች ለጉዳዩ ከፍ ያለ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አሳስቧል።

የደቡብ አፍሪካ ከተማ የሆነችው ኬፕታውን ባለሥልታናት በቅርቡ እንዳስጠነቀቁት ዝናብ ካልዘነበ በመጪው ነሃሴ ወር ላይ በከተማዋ ያሉ የውሃ መስመሮች የውሃ አቅርቦታቸው ይቋረጣል።

ከተማዋ የገጠማት የውሃ እጥረት በምድራችን ላይ ያለው የውሃ ሃብት ምንያህል ለአደጋ እንደተጋለጠ የሚያሳይ ነው ተብሏል።ነገር ግን ንፅህናው የተጠበቀ የውሃ አቅርቦትን የማያገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የምድራችን ነዋሪዎች የገጠማቸው ስጋት፤ የኬፕታውን ከተማ ከገጠማት ችግር በእጅጉ የከፋ እንደሆነ ተነግሯል።

ተያያዥ ርዕሶች