የአፍሪካ ሃገራት ነፃ የንግድ ዝውውር ለማድረግ ተስማሙ

በኬፕ ታውን ደቡብ አፍሪካ የሚሠሩ ሴቶች Image copyright Getty Images

44 አፍሪካዊ ሃገራት በዓለማችን ትልቁ ሊባል የሚችለውን ነፃ የንግድ ዝውውር ስምምነት በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ በፊርማቸው አፅድቀዋል።

በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራ ላይ እንደሚውል ተስፋ የተጣለበት ይህ ስምምነት 1.2 ቢሊዮን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገምቷል።

ሆኖም ግን ናይጄሪያን ጨምሮ ሌሎች 10 የአፍሪካ ሃገራት ይህን ስምምነት ለመፈረም አልፈቀዱም። ስምምነቱ እውን እንዲሆንና ተፈፃሚነቱ እንዲረጋገጥ 54ቱም የአፍሪካ ሃገራት ፊርማቸውን ማሳረፍ ይኖርባቸዋል።

በእንግሊዝኛው 'አክፍታ' በሚል ምህፃረ ቃል እየተጠራ ያለው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ዝውውር ስምምነት በአፍሪካ ሃገራት መካከል ድንበር የማያግዳቸው የንግድ ልውውጦች እንዲካሄዱ እንደሚያዝ እየተነገረ ይገኛል።

አልፎም ግብር እና አስመጭዎች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ በማስቀረት በአህጉሪቱ ሃገራት መካከል ያለውን ነፃ ዝውውር ያበረታታል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ጥቅሙን ያስረዳሉ።

ማዕቀፉ በዋናነት የአፍሪካ ሃገራትን የእርስ በርስ ንግድ ለማበረታታ ያቀደ ይሁን እንጂ የሥራ ዕድሎች መፍጠርም ትልቁ የስምምነቱ ትሩፋት እንደሚሆን ተገምቷል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የወቅቱ ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ስምምነቱን ''መልካም ፈተና" ሲሉ ቢጠሩትም "የስኬት ጥማት እንዲኖረንና ድፍረት እንድናዳብር ኃይል ይሰጠናል" ብለዋል።

ለስምምነቱ መሳካት የአህጉሪቱ ሃገራት ''ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ ይኖርባቸዋል'' ሲሉም አሳስበዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ዝውውር ቀጣና ምንድነው?

ጥምረት ለአፍሪካ

አፍሪካ ውስጥ የእርስ በርስ ንግድ እጅግ አናሳ ሲሆን በአህጉሪቱ ከሚደረገው አጠቃላይ ንግድ 10 በመቶውን ብቻ የሚይዝ ነው። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚገኙ ሃገራት እርስ በርስ ከሚያደርጉት 25 በመቶ ንግድ ጋር አንኳ ሲነፃፀር በጣም ዝቅ ያለ ነው።

የንግድ ስምምነቱ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ትልቁ ዓላማ የአውሮፓ ሕብረት የሚከተላቸውን የጉምሩክ ጥምረት፣ ማዕከላዊ ገበያ፣ አልፎም አንድ የመገበያያ ገንዘብ መመስረትን የመሳሰሉ እርምጃዎችን መውሰድ ነው። ይህ እውን ይሆን ዘንድ ግን በርካታ እንቅፋቶች መወገድ እንዳለባቸው ሁሉም የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

አንደኛው ፈተና ጥሬ ዕቃዎችን ለተቀረው ዓለም በማቅረብ የምታወቀው አፍሪካ የምርት መጠን አነስተኛ መሆኑ ነው። ሌላኛው ደግሞ የምጣኔ ሃብት አቅማቸው ጠንካራ የሆኑ እንደ ናይጄሪያ የመሳሰሉ ሃገራትን ወደ ስምምነት መጥራት ነው።

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የስምምነቱ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ የንግድ ማሕብራት ስለማዕቀፉ በቅድምያ እንዳላማከሯቸው በመናገር ሃገራቸው በስምምነቱ ያልተሳተፈችበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ሌሎች ፊርማቸውን ያላሳረፉ ሃገራት በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ሰምምነቱን እንደሚፈርሙ ተስፋ እንዳለው የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

ተያያዥነት ያላቸው የኢንተርኔት ማስፈንጠሪዎች

ቢቢሲ ለሌሎች የኢንተርኔት ገጾች ኃላፊነት አይወስድም