እውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ አለው?

እውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለኢትዮጵያ ይጠቅማል? Image copyright Getty Images

በሩዋንዳዋ ዋና ከተማ ኪጋሊ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችና የሃገራት ተወካዮች አህጉሪቱን በነፃ የንግድ ልውውጥ ሊያስተሳስር የሚችል ስምምነትን ፈርመዋል።

ስምምነቱ 1.2 ቢሊዮን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ለሃገራት ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ እንዳለው እየተነገረም ይገኛል።

እንደ አውሮፓ ሕብረት ዓይነት ቅርፅ ይዞ ለመንቀሳቀስ እያሰበ ያለው ይህ ቀጣና በአፍሪካ ሃገራት መካከል ድንበር የማያግዳቸው የንግድ ልውውጦች እንዲካሄዱ እንደሚያዝ፤ አልፎም ግብር እና አስመጭዎች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ በማስቀረት በአህጉሪቱ ሃገራት መካከል ያለውን ነፃ ዝውውር እንደሚያበረታታ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 የአፍሪካ ሃገራት ስምምነቱ ይጠቅመናል ብለው ቢፈርሙም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የአፍሪካ ሃገራት በእኩል የዕድገት ደረጃ ላይ አለመሆናቸው ለማዕቀፉ ተፈፃሚነት ትልቅ እንቅፋት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍና ንግድ፣ ግብር፣ ፋይናንስና ኢንቨስትመንት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍሰሃ-ፅዮን መንግሥቱ አንዱ ሲሆኑ ከስምምነቱ ቀድሞ መምጣት ያለበት ነገር እንዳለ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"በጠቅላላቅ የአፍሪካን ሆነ የኢትዮጵያን ገበያ ሳናሳድግ አንድ ማዕከላዊ ገበያ መመስረታችን ጥቅሙ ለማን ነው?" በማለት ይጠይቃሉ ምሁሩ። ስምምነቱ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንደሌላቸው የሚያስረግጡት ፕሮፌሰር ፍሰሃ ከማዕቀፉ በፊት ሊሰሩ የሚገቡ በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ።

"ቪሳ እንኳን ለማግኘት ችግር በሆነበት አህጉር ይህ ስምምነት ላይ መድረስ ትንሽ ችኮላ የበዛበት ይመስለኛል። እንደእኔ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር ውሳኔ ነው መወሰን ያለባቸው። ለሃገራችን ተስማሚ ሆኖ ካልተገኘ አንቀበለም ማለት መቻል አለባቸው። ማንኛውም ስምምነት ሲደረግ መለኪያው መሆን ያለበት አሁን ላለው እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ያለው በጎ አስተዋፅኦ ነው" ባይ ናቸው ምሁሩ።

Image copyright Getty Images

ነፃ የንግድ ቀጣናው ለኢትዮጵያዊያን አምራቾች የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው? ጉዳቱስ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄ ፕሮፌሰር ፍሰሃ ምላሽ ሲሰጡ "ለምሳሌ ኬንያን እንመልከት። በቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪና በሰለጠነ የሰው ኃይል ከኛ የተሻሉ ናቸው። ወደእኛ ሃገር መጥተው ንግድ የሚያከናውኑ ከሆነ በእርግጠኝነት የእነሱ ጥቅም እንጂ የእኛ ጥቅም አይከበርም። ለአምራቹም ጉዳቱ የሚያመዝ ነው የሚሆነው።"

"መሆን ያለበት ለእኛ ከሚበጁ ጋር አብሮ መስራት እንጂ ሁሉንም እሺ ብለን የምንቀበል ከሆነ ዘላቂ የሆነ ጥቅም አናገኝም፤ የሃገራችን አምራቾችም አይጠቀሙም" ይላሉ።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የወቅቱ ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው ስምምነቱን ''መልካም ፈተና" ሲሉ ቢጠሩትም "የስኬት ጥማት እንዲኖረንና ድፍረት እንድናዳብር ኃይል ይሰጠናል" ብለዋል። ለስምምነቱ መሳካት የአህጉሪቱ ሃገራት ''ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ ይኖርባቸዋል'' ሲሉም አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ኮሚሽን ስምምነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ''በዚህ ስምምነት 80 በመቶ በሚሆነው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት እንዲሁም 70 በመቶ መደበኛ ያልሆነ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እና ወጣቶች ዋነኛ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ይላል።

ሆኖም ግን ናይጄሪያን ጨምሮ ሌሎች 10 የአፍሪካ ሃገራት ይህን ስምምነት ለመፈረም አልፈቀዱም። ስምምነቱ እውን እንዲሆንና ተፈፃሚነቱ እንዲረጋገጥ 54ቱም የአፍሪካ ሃገራት ፊርማቸውን ማሳረፍ ግድ ይላቸዋል።