ሴቶች በሰሜን ኮሪያ ሠራዊት ውስጥ

በያሉ ወንዝ ዳርቻ አነድ የሰሜን ኮሪያ ሴት ወታደር ጠመንጃዋን እንደያዘች ካሜራውን ታያለች Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በያሉ ወንዝ ዳርቻ አነድ የሰሜን ኮሪያ ወታደር

የቀድሞ ወታደሯ እንደተምትናገረው በዓለማችን ትልቁ ወታደራዊ ኃይል ውስጥ መሆን ለሴት በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች የወር አበባቸው ማየት ያቆሙ ነበር። መደፈር ደግሞ አበረዋት ካገለገሉት መካከል ለብዙዎቹ እውነታ ነበር።

ለ10 ዓመታት ሊ ሶ ዬዎን ከ20 በላይ ከሚሆኑ ሴቶች ጋር በምትጋራው መኝታ ቤት ተደራራቢ ከሆነው አልጋ ታችኛው ላይ ነበር የተምትተኛው። እያንዳንዳቸውም ዩኒፎረማቸውን የሚያስቀምጡበት መሳቢያ ነበራቸው።

ከወታደር ቤት ከወጣች ከአሥር ዓመት በላይ ቢሆናትም የነበረውን ሁኔታ ከኮንክሪቱ ሽታ አንስቶ ታስታውሳለች። ''ያልበናል። የምንተኛበት ፍራሽ ከጥጥ የተሰራ ስላልሆነ የላብና ሌሎች ሽታዎች ይፈጠራሉ። ደስ አይልም'' ትላለች።

ለዚህም የዳረጋቸው የማጠቢያ ቦታው ችግር ነው። ''ሴት እንደመሆኔ በጣም ከባድ ሆኖ ያገኘሁት እንደፈለግን ገላችንን መታጠብ አለመቻላችን ነው'' ትላለች ሊ ሶ ዬዎን ።

Image copyright Shutterstock

ሊ ሶ ዬዎን አሁን 41 ዓመቷ ሲሆን ያደገችው በሃገሪቱ ሰሜን አካባቢ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ልጅ ናት። የቤተሰቧ ወንድ አባላት ብዙዎቹ ወታደር ነበሩ። እ.አ.አ በ1990 በሃገሪቱ ረሃብ ሲከሰት ቢያንስ በቀን አንዴ መብላት እንደሚቻል በማሰብ ነበር ወታደራዊ ኃይሉን ለመቀለቀል የወሰነችው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችም በተመሳሳይ ምክንያት ወታደር ሆነዋል።

''ረሃቡ በተለይ ለሴቶች ጊዜውን በጣም ከባድ አድርጎት ነበር'' ይላል የ'ኖርዝ ኮሪያ ሂድን ሬቮሉሽን' ደራሲ የሆነው ጂውን ቤክ። በመቀጠልም ''ብዙ ሴቶች የሠራተኛውን ኃይል መቀላቀል ነበረባችውና በዚህም ወቅት ለፆታዊ ጥቃትና ለሌሎችም ችግሮች ተጋልጠዋል'' ብሏል።


የሸሹትን ማመን

ጁሊዬት ሞሪሎ እና ጀኢውን ቤክ የሊ ሶ ዬዎን ትውስታዎች ከብዙዎች ትውስታ ጋር እንደሚመሳሰል ቢያረጋግጡም የሸሹትን ግን ማመን በጥንቃቄ ነው ይላሉ።

ቤክ እንደሚሉት ''ስለ ሰሜን ኮሪያ ማወቅ በጣም ይፈለጋል። በተለይ የገንዘብ ድጋፍ ካለው ሰዎች የተጋነኑና ከእውነታው የራቁ ታሪኮችን ለሚድያ ለመዘገብ ይገፋፋሉ። ሸሽተው በሚድያ መታየት የማይፈለጉትን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።''

ከሰሜን ኮሪያ ምንጮች የሚመጣው መረጃ ደግሞ ፕሮፖጋንዳ ነው። ሊ ሶ ዬዎን ግን ከቢቢሲ ጋር ላደረገችው ቆይታ ምንም ዓይነት ክፍያ አልተሰጣትም።


በመጀመሪያ ሊ ሶ ዎን ያኔ የ17 ዓመት ወጣት የነበረች ሲሆን በሃገር ፍቅርና በአብሮ መሥራት ስሜት እየተገፋፋች በጣም ደስተኛ ነበረች። ብዙም ባትጠቀምበትም የፀጉር ማድረቂያ ሳይቀር መኖሩ በጣም እንደትገረም አድርጓት ነበር።

የዕለተለት እንቅስቃሴዎች ለወንድም ለሴትም አንድ ዓይነት ነበሩ። ሴቶች ከወንዶች ይልቅ አጠር ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ቢኖራቸውም እንደ ፅዳት፣ ልብስ አጠባ፣ ምግብ ማብሰልና ሌሎች ሥራዎችን እንዲሠሩ ይጠበቅባቸው ነበር።

''ሰሜን ኮሪያ በባህሉ በወንድ የሚመራ ማህበረሰብ በመሆኑ ባህላዊ የፆታ ክፍፍል አለ'' ትላለች በፈረንሳይኛ የተጻፈው የ'ኖርዝ ኮሪያ 100 ክዌስችንስ' ደራሲ ጁሊዬት ሞሪሎ። ቀጥላም '' ሴቶች እስካሁን እንደ 'ቱኮንግ ኡንጄዎንግሱ' ነው የሚታዩት ይህ ደግሞ ቃል በቃል 'የድስት ክዳን መሪ' ማለት ሲሆን ሴቶች ምንጊዜም በማዕድ ቤት መቅረት እንዳለባቸው መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።

ከባዱ ሥልጠናና ምግብ ማከፋፈሉ የሊ ሶ ዬዎንና የአጋሮቿን ሰውነት ጎድቶት ነበር።

''በገባን ከ6 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በምግቡ አለመመጣጠንና በጭንቀት ምክንያት የወር አበባችን መምጣት አቆመ'' ትላለች።

''ብዙ ሴት ወታደሮች የወር አበባቸው ባለመምጣቱ ደስተኛ ነበሩ። ምክንያቱም ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ በመሆናቸው በዚያ ላይ ወር የአበባ ቢጨመርበት ይበልጥ ከባድ ይሆንብን ነበር'' ብላለች።


ሊ ሶ ዬዎን ለወር አበባ መጠበቂያ ምንም ነገር እንደማይሰጣቸውና ብዙዎቹ የተጠቀሙባቸውን ፓዶች በድጋሚ ለመጠቀም ይገደዱ እንደነበር አስረድታለች።

''ሴቶች እስከ ዛሬ ባህላዊውን ነጭ የጥጥ ፓድ ነው የሚጠቀሙት'' የምትለው ጁሊዬት ቀጥላም ''ማታ ማታ ወንዶች በማያዩበት ጊዜ ነው መታጠብ ያለባቸው። ለዚህም በሌሊት እየተነሱ ያጥቡ ነበር።'' ጁሊዬት ያነጋገረቻቸው ሴት ወታደሮች የወር አበባቸው እንደማይመጣ ነግረዋታል።

Image copyright Sipa Press/REX/Shutterstock

ሊ ሶ ዬዎን ወታደራዊ ኃይሉን በፈቃደኝነት ትቀላቀል እንጂ በ2015 ከ18 ዓመት በላይ ያሉ ሴቶች በሙሉ 7 ዓመት የወታደራዊ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ተደንግጓል።

በዚያን ጊዜም የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ያልተለመደ እርምጃ በመውሰድ ለሴት ወታደሮቻቸው 'ዳይዶንግ' የሚባለውን አንደኛ ደረጃ የወር አበባ መጠበቂያ ፓድ እንደሚያከፋፍል አሳወቋል። ''ይህን እርምጃ የወሰዱት የቀድሞ ስተታቸውን ለማረም ይሆናል'' ይላል ጂውን ቤክ።

ቀጥሎም ''ይህ መግለጫ የተሰጠው በጊዜው የነበረው የሴት ወታደሮች ሁኔታ መጥፎ እንደነበር በመታወቁ ሞራላቸውን ለመጠበቅና ለሴቶች 'ካሁን በኋላ እንክብካቤ ይኖረናል' ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ ነው'' ብሏል።

'ፒዮንግ ያንግ ፕሮዳክትስ' የተሰኙም የውበት ዕቃዎች በቅርቡ ለአየር ኃይል ሴት አብራሪዎች ተከፋፍሏል። ይህም በ2016 ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያ የውበት ዕቃዎች አንደ ሻኔል፣ ዲዮር እና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ስመጥር ዕቃዎች ጋር መዳደር መቻል አለባቸው ካለ በኋላ ነበር።

ይህም ሆኖ ግን በክፍለ ሃገር የተመደቡ ሴት ወታደሮች አብዛኞቹ የተለየ መፀዳጃ ቤት እንኳን የላቸውም። ለጁሊዬት እንደነገሯት አንዳንዴ ከወንዶች ጋር መፀዳጃ ቤት መጠቀም እንደሚገደዱ ይህም አደጋ ላይ ሊጥላቸው እንደሚችል ይናገራሉ።


ጂውንና ጁሊዬት እንደሚናገሩት የፆታ ትንኮሳ በጣም የተለመደ ነው። ጁሊዬት ሴት ወታደሮቹን ስለ መደፈር በጠየቀችበት ጊዜ ሁሉም ''ሌሎችን ያጋጥማል'' እንጂ ማናቸውም አጋጥሞናል ብለው እንዳልነገሯት ገልፃለች።

''የቡድኑ ኮማንደር በቡድኑ ክፍል ውስጥ ባለው መኝታ ቤቱ ከሰዓት እላፊ በኋላ በመቆየት በእርሱ ሥር ያሉት ሴት ወታደሮች ይደፍራል። ይህም በተደጋጋሚ ያለማለቂያ ነበር የሚፈጸመው'' ትላለች።

የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል የፆታ ጥቃትን እንደማይቀበሉና ለደፈረ ወታደር ደግሞ እሰከ 7 ዓመት እስራት እንደሚቀጡ ይናገራል። ''ብዙ ጊዜ ግን ማንም ሰው ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደልም። ስለዚህ ወንዶቹ ሳይቀጡ ያልፋል'' ትላለች ጁሊዬት።

Image copyright Reuters

አክላም በወታደራዊ ኃይል ውስጥ የፆታ ጥቃትን በተመለከተ ያለው ዝምታ በሰሜን ኮሪያ ከሰፈነው ጥልቅ አባዊነት አመለካከት የመጣ ነው። ይህም ነው ሴት ወታደሮች የፅዳትና ምግብ ማብሰልን እንደሠሩ የሚያደርገው ትላለች።

ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚመጡ ሴቶች በተለይ የምህንድስና ብሪጌድ ውስጥ የሚቀጠሩ ሲሆን፤ መደበኛ ባልሆኑ ጎጆ ቤቶች ውስጥ ስለሚያስቀምጧቸው አደጋ ላይ ይወድቃሉ።

''በቤት ውሰጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶች አይወገዙም ስለዚህም ይፋ አይወጡም፤ በወታደራዊ ሥርዓት ውስጥም ያው ነው። አጥብቄ ግን መናገር የምፈልገው በደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል ውስጥም ተመሳሳይ የሆነ ባህል ነው ያለው'' ትላለች።

ሊ ሶ ዬዎን ሳጂን ሆና ያገለገለችው በደቡብ ኮሪያ ጠረፍ ላይ የነበረ ሲሆን፤ 28 ዓመት ሲሞላት ነበር ለቃ የወጣችው። ከቤተሰቧ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት በመቻሏ ደስ ቢላትም ከውትድርና ውጪ ላለው ሕይወት ግን ዝግጁ የነበረች አልመሰላትም። ምክንያቱም የገንዘብ ችግር ገጥሟት ስለነበረ ነው።

እንደ አውሮፓዊያኑ በ2008 ነበር ወደ ደቡብ ኮሪያ ለማምለጥ የወሰነችው። በመጀመሪያ ሙከራዋ በቻይና ጠረፍ ላይ ተይዛ ለአንድ ዓመት ታስራለች። ከእስር ቤት እንደተለቀቀችም በሁለተኛ ሙከራዋ ቱሜን የሚባለውን ወንዝ በዋና አቋርጣ በቻይና በኩል ወደ በደቡብ ኮሪያ ለመግባት ችላለች።