የሚቀያየረው የከባቢ አየር ሁኔታ የሰው ልጅን ዝግመተ ለውጥ መርቷል

ኦሎርጌዛይዪ በ64 ኪሎሜትር ካሬ ላይ ያረፈው የቁፋሮ ቦታ

የምስሉ መግለጫ,

ኦሎርጌዛይዪ በ64 ኪሎሜትር ካሬ ላይ ያረፈው የቁፋሮ ቦታ

የሰው ልጅ ከዛሬ 100 000 ዓመታት ቀድም ብሌ ማህበራዊ ተግባቦትና መነገድን ሳያዳበሩ አይቀርም ሲሉ ተመራማሪዎች ገለፁ።

ይህ የተገለፀው ሳይንስ በተሰኘውመጽሔትና ድረ-ገጽ ላይ በታተሙ ተከታታይ ጥናቶች ነው።

ውጤቶቹም የተገኙት በኬንያ ሪፍት ቫሊ ላይ ቅሪተ አካል ጥናት በሚደረግበት ስፍራ ሲሆን፣ ቦታውም 'አንድ ሚሊዮን ዓመታትን' እድሜ ያስቆጠረ ነው ይላሉ ከሰሚትሶኒያን ተቋም በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ሪክ ፖትስ።

የተለያዩ መሣሪያዎች መሠራታቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።

ኦሎርጌዛይዪ በተሰኘው የቁፋሮ ቦታ ላይ በጊዜው የነበሩት አካባቢያዊ ለውጦች ሆሞ ሳፕየንስ የተሰኘውን ጥንታዊ የሰው ልጅ እድገት አንዲያደርግ ግፊት ሳያደርጉ አይቀርም።

ዓለም ስትገለበጥ

የቀድሞ ሰዎች በአካባቢው የነበሩት ወደ 700ሺህ ዓመታት ቀደም ብለው ሲሆን በአካባቢው ከሚገኙ ድንጋዮች በእጅ የሚያዙ መጥረቢያዎችን ይሠሩ እንደነበር ዶ/ር ሪክ ያስረዳሉ።

''[ከቴክኖሎጂ አንፃር ሲታይ] ነገሮች በጣም ቀስ ብለው ነው የተለዋወጡት፤ እሱም ሺህ ዓመታትን ፈጅቷል'' ይላሉ።

ከዚያም ቢያንስ ከ500 ሺህ ዓመታት በፊት ትልቅ ለውጥ መጣ።

አካባቢውን በአንዴ አስደንጋጭ ቴክቶኒክ መነቃነቅና ያልተለመደ የከባቢ አየር መለዋወጥ አናወጠው። የመሬት መሸርሸር ደግሞ ወደ 180 ሺህ ዓመታት ገደማ የሚያህል የጂዎሎጂ ምልክቶችን አጥፍቷል።

የተቀያየረው መልከአምድሩ ብቻ አልነበረም ። በአካባቢው የነበሩትን እፅዋትና እንስሳትንም ጭምር ቀይሯል። ይህም ደግሞ በዚያን ጊዜ ለነበሩት ሰዎች የነበሩትን ግብዓቶች ቀይሯል ማለት ነው።

የምስሉ መግለጫ,

በቁፋሮው የተገኘው ግኝት የነበረውን የአየር መለዋወጥ አፈሩ ከደረቅ ወደ እርጥብ በመቀያየሩ እንደሆነ አሳይቷል

ምልክቶቹ መልሰው መታየት ከሚጀምሩበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ በጊዜው የነበሩት ሰዎች ሕይወት በጣም ተቀያይሮ ነበር።

''የነበረው የለውጥ ፍጥነቱ በጣም የሚደንቅ ነው'' የሚሉት ዶ/ር ሪክ ''በክፍተቱ ዘመን ቅጽበታዊና ፈጣን ዝግመተ ለውጦች ነበሩ'' ብለዋል።

የባልጩት መንገድ

በዚህ ዘመን አዳዲስ መሣሪያዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ከባልጩት የተሠሩ ትንሽ፣ ስል ቢላና እንደ ጩቤ የሾሉ መሳሪያዎች መታየት ጀመሩ።

ይህ የቴክኖሎጂ እድገት መዓከላዊ የድንጋይ ዘመን በመባል የሚታወቀው የዝግመተ ለውጥ ዘመን ነው በማለት ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ኤሌኖር ሼሪ ያስረዳሉ።

ከፍልጥ ድንጋይ የእጅ መፍለጫ ከመሥራት ይልቅ ትናንሽና ስል ወደሆኑ ቅርጾች ተዘዋወሩ። እነዚህንም በረዥም እንጨቶች ላይ በመስቀል እንደ አደን መሣሪያ ይጠቀሙባቸው ነበር።

በኦሎርጌዛይዪ አካባቢ የነበሩት ሰዎች 98% ይጠቀሙባቸው የነበሩት ድንጋዮች ከአካባቢያቸው በ 5 ኪ.ሜ ዙሪያ ከሚያገኙት የባልጩት ድንጋዮች ነበር።

ሰዎቹ እነዚህን ድንጋዮች የሚያገኙት ከ 25 ኪ.ሜ እስከ 95 ኪ.ሜ ገደማ በእግር እየተጓዙ ነበር። በተጨማሪም ዶ/ር ሪክ በጊዜው ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ይገናኙ እንደነበር ያስረዳሉ።

ይህንን ቦታ በታሪክ የረዥም ርቀት ጉዞና የንግድ ምልክት ምሥክር ያደርገዋል።

የምስሉ መግለጫ,

(ከግራ ወደ ቀኝ) የእጅ መፍለጫ፣ ስል ባልጩት፣ በቁፋሮ የተገኙ የቀለም ምልክቶች

ተጨማሪ ማስረጃዎች በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ከ20 እስከ 25 ብዛት የነበራቸው እንደነበርና ቡናማ ቀለማት ይጠቀሙ እንደነበር ያሳያሉ። እነዚህ ለሥራ ብቻ የይሁን ወይንም ማህበራዊ ሚና ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም።

ዶ/ር ማርታ ሚራዞን ላር ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ የተደረገውን የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ለመረዳት ኦሎርጌዛይዪ ጠቃሚ ቦታ ነው፤ ምክንያቱም የእሳተ ጎሞራን ቅሪት በማጥናት ''ትክክለኛ ቀናት''ን ለማግኘት ይረዳል።

ሰው ልጅ አመጣጥ

ዶ/ር ኤሌኖር በጥናቱ ላይ ያልተሳተፉ ሲሆን አጥብቀው '' መካከከላዊ የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂ በምሥራቁም በምዕራቡም አፍሪካ እኩል ጊዜ ላይ'' እንደመጣ ይናገራሉ።

የተፈጥሮዓዊ ሚዩዚየም የሆኑት ፕሮፌሰር ክሪስ ስትሪንገርም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

''ይህ መካከለኛው የድንጋይ ዘመን አንድ ቦታ ላይ ጀምሮ ወደ ሌላው ከመስፋፋት ይልቅ በተለያዩ የአፍሪካ ቦታዎች ላይ ከ315 000 ዓመታት ጀምሮ እኩል ጊዜ ላይ መጀመራቸውን እንዳስብ አድርጎኛል'' ብለዋል።

በኬንያ የነበረው ቁፋሮ ላይ የተገኙት ምልክቶች ባህሪ የሆሞ ሳፕየንስ ቢሆንም ሃሳቡን የሚደግፍ ቅሪተ አካላት በጊዜውና በቦታው ላይ አልተገኘም።

የዓለማችን የጥንቱ ሆሞ ሳፕየንስ የተገኘው በሞሮኮ ሲሆን የተገኙት ቅሪተ አካላት ከ350 000 ዓመታት በፊት የነበሩ ናቸው።