ካለሁበት 27፡ 'እንጀራ ከበላሁ ዓመት አልፎኛል'

ዲላይት ጌታቸው

ዲላይት ጌታቸው እባላለሁ። ነዋሪነቴንም በጊዜያዊነት በቪዬትናም ባለችው ሙይኔይ ከተማ አድርጌያለሁ።

ወደዚህ የመጣሁት በአጋጣሚ ነው። መጀመሪያ የመጣሁት ታይላንድ ሲሆን ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ነበር ቪየትናም ቅርብ በመሆኗ ለጉብኝት ወደዚህ ያቀናሁት።

እንደደረስኩ ያረፍኩባት በቪየትናም መዲና ሐኖይ ነበር። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ሆ ቺ ሚን የምትባለው ሌላኛዋ የቪየትናም ከተማ መጣሁ።

በመቀጠልም ሙይኔይን ስጎበኝ በጣም ወደድኳት እናም እዚሁ ለመቆየት አሰብኩ።

እንደ አጋጣሚም ሆኖ የነበርኩበት ማረፊያ ውስጥ ደግሞ የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ያስፈልጋቸው ስለነበር፤ እዚያው እያገለገልኩኝ ለመቅረት ወሰንኩኝ። ይሄው መኖሪያየን ሙይኔይ ካደረግኩ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል።

ሙይኔይን ከአዲስ አበባ ጋር ሳነፃጽራት ከምግቡ አንስቶ፣ የኑሮው ዘዬ ሰዎቹ የተለያዩ ናቸው። ቪየትናም በጣም የተለየች ሃገር ናት።

ሆኖም ግን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ለእኔ ትናንሽ ሱቆቹና ሱቅ በደረቴዎቹ ናቸው። በተለይ ይህ ጉዳይ ከናዝሬት ጋር ይመሳሰልብኛል።

ከምግባቸው ደግሞ በጣም የምወደው አትክልትና ሥጋ ወይም አትክልትና የዓሣ ዓይነቶችን አቀላቅለው የሚሰሩትን ሾርባ 'ፈ' ተብሎ የሚጠራውን ነው።

በተለይ የሚያቃጥል አዋዜ ነገር ቢጨምሩበት ደግሞ ጣዕሙ የተለየ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በጣም ትናፍቀኛለች። እንጀራ በዓይኔ ውል ውል ይላል። ይሄው እንጀራ ከበላሁ ዓመት አልፎኛል።

ሬስቶራንት ሄጄ እንዳልበላ በቅርብ ያለው የኢትዮጵያ ምግብ ቤት የሚገኘው ካምቦዲያ ነው።

እናም እንዳማረኝ እንጀራ በዓይኖቼ እንደዞረ ነው።

የምስሉ መግለጫ,

ዲላይት የምትሠራበት ካምፕ

የምሠራበት ቦታ ትንንሽ ድንኳኖችን ለቱሪስቶች የሚያከራይ የእንግዳ መቀበያ ቦታ (ካምፒንግ) ሲሆን ጥዋት ከእንቅልፌ ነቅቼ ካለሁበት ድንኳን ስመለከት የሚታየኝ አረንጓዴ መሬትና ዛፎች ናቸው።

እኔ በሕይወቴ እንደዚህ በድንኳን ውስጥ ኖሬ አላውቅም ነበር ቢሆንም ለየት ያለ አኗኗር ዘይቤ ነውና ደስ ይላል።

ይህ ብቻ አይደለም ለየት የሚለው እኔ ራሱ በዚህ ሀገር እንደ ልዩ ፍጥረት ነው የምታየው። ኢትዮጵያ እያለሁ ዘወር ብሎ የሚያየኝ ሰው የለም።

ምናልባት ብዙ ከአፍሪካ የሚመጡ ሰዎችን አይተው ስለማያውቁና በክፋት ላይሆን ይችላል ብየ ባስብም የሚያፈጡበት ሁኔታ ያስደንቀኛል።

ታይላንድ በነበርኩበት ወቅት ከተለያየ ዓለም ክፍል የሚመጡ ቱሪስቶች መናሀሪያ በመሆኗ ልዩነትን ማስተናገድ ችለዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ዲላይት የእንግዶችን ውሻ በባሕር ዳርቻ ስታንሸራሽር

መጓዝ ስለምወድ እቃየን በሙሉ በአንድ በጀርባ በሚታዘል ትልቅ ቦርሳ በመያዝ ለባለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ ሀገሮች ሄጃለሁ።

ከሁለት ወይም ሶስት በስተቀር ኢትዮጵያውያን አላጋጠሙኝም ከዚህ ተነስቼ የተረዳሁት ብዘ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን እንሌሉ ነው።

ለክሪሰቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦