አብረሃም መብራቱ፡ የየመንን ብሔራዊ ቡድን ለትልቅ ውድድር ያበቃ ኢትዮጵያዊ

አብረሃም መብራቱ
የምስሉ መግለጫ,

አብረሃም መብራቱ

በጦርነት የተመሳቀለችው የመን እ.አ.አ በ2019 ጥር ወር በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ለሚዘጋጀው ለእስያ ዋንጫ ፍፃሜ ማለፏ ታላቅ ደስታን ፈጥሯል። ይህም በየመን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን እውን የሆነውም በኢትዮጵያዊው አብረሃም መብራቱ አሠልጣኝነት ነው።

የአሠልጣኝ አብረሃምና ተጫዎቾቹ ወደ ፍፃሜው ጨዋታ ማለፋቸውን ያወቁት በማኒላ በተደረገው ግጥሚያ ፊሊፒንስ ታጂክሰታንን 2 ለ 1 ካሸነፈች በኋላ፤ የመንም ኔፓልን በተመሳሳይ ውጤት በኳታር መዲና ዶሃ ስታሸንፍ ነው።

ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ የቡድኑን አመራር የተረከበው አብረሃም ቡድኑ አንዴም ሽንፈትን ሳይቀምስ ነው ወደ አህጉራዊ ውድድር ለመግባት የቻለው። በካፍ የአስልጣኝነት እውቅና ያለው አብረሃም ለቢቢሲ ስፖርት እንደተናገረው የመን ያልተጠበቀውን ድል በመግኘቷ ደስታው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጿል።

''ይህንን ብሔራዊ ቡድን አሰልጥኜ ለእስያ ዋንጫ እንዲያልፍ ለማድረግ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለየመን የመጀመሪያዋ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆኖ ለመቅረብ የተደረገው ጉዞ በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ ቢሆንም ትልቁ እርምጃ ተራምደናል'' ብሏል።

በኢንዱሔም ቢን ሐማድ ስቴድየም ለየመን የማይረሱትን 2 ግቦችን በኔፓል ላይ ያስቆጠረው አብዱልዋስያ አልማታሪ ነው። አብረሃም ከአምስት ዓመት በፊት በእስያ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የመንን ቡድን አሰልጥኖ የነበረ ሲሆን፤ ይህ ድል በጦርነት ለተመሳቀለችው ሃገር ደስታን የሚፈጥር ምክንያት እንደሚሆን ይናገራል።

የምስሉ መግለጫ,

አብረሃም መብራቱ

''በየመን ጦርነት እየተካሄደ ስለሆነ ላለፉት አራት ዓመታት ምንም የሊግ ውድድር አልነበረም። ይህ ሁኔታዎችን በጣም አስቸጋሪ ከማድረጉ የተነሳ ለዚህ ማጣሪያ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰባሰብ ትልቅ ፈተና ገጥሞኝ ነበር። በስተመጨረሻ ግን እሰከ ፍፃሜ መሄድ የሚችል ጥሩ ቡድን ለማደራጀት ችለናል። በሜዳችን መካሄድ የነበረባቸውንም ጨዋታዎች በሙሉ በሌላ ሃገር ሜዳ መጫወት የተገደድን ቢሆንም፤ ቢያንስ በእንደዚህ ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ የየመንን ሕዝብ ማስደሰት ችለናል። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ልፋቴ ውጤታማ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ'' ብሏል አብረሃም ።

ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ባዳበረው የማሰልጠን ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖችን ከማሰልጠኑ ባሻገር፤ አብረሃም ታዋቂ የእግር ኳሱ ተጫዋችም ነበረ። ከሁለት ዓመት በፊት የብሔራዊ ቡድኑን የአሰልጣኝነት ሃላፊነት ከመረከቡ በፊት የየመን እግር ኳስ ማህበር የቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆን ሰርቷል። አብረሃም ለኢትዮጵያዊያን አሠልጣኞች የካፍ የአሠልጣኝነት ስልጠናን በመስጠትም ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያዊ አሰልጣን የሌላ ሃገርን ቡድንን በመምራት ለትልቅ የውድድር መድረክ ሲያበቃ የአብረሃም ስኬት በታሪክ የመጀመሪያው ነው። ምንም እንኳን አብረሃም ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን በመምራት ስኬት ያደርሳል ተብሎ ተጠብቆ ነበረ።