ካለሁበት 26 ፡ 'እዚህ አራስ፣ መታረስና ማረስ ብሎ ነገር አያውቁም'

ሶፊያ እባላለው ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነኝ። ስዊድን የመጣሁት በጋብቻ ሲሆን እዚህ ከመጣሁ አምስት ዓመት ሊሆነኝ ነው።

እዚህ አኗኗሩ ትቼው ከመጣሁትና ማህበራዊ ትስስሩ ጠንካራ ከሆነበት ባህል የሚለይ በመሆኑ መጀመሪያ ላይ ብቸኝነቱና የአኗኗር ዘዬውን መልመድ ቸግሮኝ ነበር።

ጉርብትና ይናፍቃል። አምስት ዓመት አንድ አፓርትመንት ላይ ነው የኖርኩት የጎረቤቶቼን ስም እንኳ አላውቅም።

ከሆላንድ ኤምባሲ ከፍ ብሎ በሚገኘው ባደግኩበት ጅማ ሰፈር ጉርብትና በጣም የጠበቀ ነበር። ከትምህርት ቤት ስመለስ እናቴ ባትኖር ጎረቤት ጋር ገብቼ ነበር የምበላው።

እኔ ስሄድ ባለቤቴ እዚህ አገር 30 ዓመት ኖሮ ነበር። እዚያ ሃገር ከልጅነቱ ጀምሮ ስለኖረና አኗኗርና ባህሉን ስለለመደው የእኔ ሃገሬን መናፈቅና የብቸኝነት ስሜቴን አይረዳውም ነበር።

ልጆቼ የተወለዱት እዚሁ ስዊድን ነው። በእርግዝናዬና ስወልድ ሁለት ነገሮችን አይቻለው። እርግዝና ክትትል ላይ ያለው ህክምናና አገልግሎት በጣም ጥሩ ነበር። በሌላ በኩል እናቴ እንድታርሰኝ ለማምጣት ሞክሬ አልተሳካልኝም።

የአራስነት ጊዜዬ በሕይወቴ ያሳለፍኩት በጣም ፈታኝ ጊዜ የነበር ሲሆን መታረስ እንደናፈቀኝ ነው የቀረው። እዚህ መታረስ፣ ማረስና አራስ ብሎ ነገር አያውቁም።

የባለቤቴ እናት ከሥራ ፍቃድ ወስዳ ልታርሰኝ ሞክራለች፤ ጠያቂዎችም ነበሩኝ ግን ሁሉም እንዳገር ቤት አልነበረም።

Image copyright Sofia

አዲስ አበባና ስቶክሆልም

ከተሞቹ ምንም የሚመሳሰል ነገር የላቸውም፤ በጣም የተለያዩ ናቸው ማለት እችላለሁ። ነገር ግን አርብ ጁምአ ዕለት ለቤቴ ቅርብ ወደ ሆነው ትልቁ የስቶክሆልም መስኪድ ስሄድ አካባቢው ላይ የማየው ድባብ የመርካቶውን አንዋርና የፒያሳውን በኒን መስኪዶች ያስታውሰኛል።

ምንም እንኳን ብዙ ሃበሻ ባይኖርም አብሮ የመስገዱ የሃገር ቤቱን ነገር ያስታውሰኛል።

በስቶክሆልም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዝግጅት ሲኖር እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን መስኪድ በማገኝበት አጋጣሚ ነው ሁሉ ነገር ሃገር ቤት የሚወስደኝ።

Image copyright Sofia
አጭር የምስል መግለጫ ሶፊያ የምትሰግድበት የስቶክሆልም ትልቁ መስጊድ

እንጀራና የሃገሩ ምግብ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ ወደ ስቶኮልም በረራ አለው ስለዚህ ሁል ቀን እንጀራ መግዛት ይቻላል። በእርግጥ በዓል ላይ ቶሎ ሊያልቅ ይችላል።

ስለዚህ የሃገሬ ምግብ ብዙ ጊዜ ቤቴ ይገኛል። በርግጥ የተገኘውን ምግብ መብላት የምችል አይነት ሰው ነኝ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ምግብ ከሌለ እዚህ አገር በብዛት የሚበላው የተፈጨ ድንች በአሳ ቤቴ ይኖራል።

ይህ ምግባቸው ደስ ብሎኝ የምመገበው ቢሆንም የተለያዩ ምግቦቻቸውን እመገባለሁ።

Image copyright Sofia

የሃገር ናፍቆት

ከኢትዮጵያ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል ከሁሉም በላይ ግን ቤተሰቤና ጎረቤቶቼ ይናፍቁኛል። ብዙ ጊዜ ሳሎን ቤቴ ሆኜ ተመስጬ የማስብበት ቦታ አለ።

ውጭ ዛፎችና ልጆች የሚጫወቱበት አነስተኛ ቦታ ይታየኛል። ዛፎቹ ስለ ወቅት ያሳታውሱኛል። በተለይም ፀሃያማ ወቅት ላይ ልጆች እዚያ ቦታ ላይ ሲጫወቱ ስመለከት ሰፈሬንና ልጅነቴን ያስታውሰኛል።

የባህል ልዩነት

በእኛ ባህል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለትልልቅ ሰዎች ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው። እዚህ ሃገር ፋርማሲው፣ ሱቁ፣ ባቡሩ፣ ሁሉ ነገር ሰልፍ ነው።

ደስ ብሏቸው ይቀመጣሉ ብዬ መቀመጫ የምለቅላቸው ወይም ሰልፍ ላይ ቅድሚያ የምሰጣቸው ትልልቅ ሰዎች ልክ አቅማቸውን የተጠራጠርኩት በሚበስል ስሜት ፊታቸውን ያኮሳትሩብኝ ነበር።

ሲደጋገም የባህል ልዩነታችንን ተረድቼ ነገሩን ተውኩት። በእርግጥ አሁንም ፊታቸውን አይቼ የደከማቸው ከመሰለኝ ጠይቄ ፍቃደኛ ከሆኑ መቀመጫም እለቃለሁ፤ ሰልፍም አስቀድማለሁ።

እዚህ ሃገር ሁሉ ነገር የተሻለና ያደገ ነው። ይህ ቢሻሻል የምለው የለም። ሆኖም ግን ትንሽ የእኛ ሃገር አይነት ማህበራዊ ህይወት በአኗኗር ዘዬው ላይ ቢጨመር ብዬ እመኛለው።

Image copyright Sofia
አጭር የምስል መግለጫ በስቶክሆልም መስጊድ መውጫ

ምኞት

የመጀመሪያ ልጄን የወለድኩበትና ከባድ የብቸኝነት ስሜት ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ብር ብዬ ሃገሬ መሄድ አለመቻሌ አሳዝኖኝ ነበር። በትክክል ሰው የተራብኩበት ጊዜ፤ በጣም የተፈተንኩበትም ጊዜ ነበር።

በተደጋጋሚ ወደ ሃገር ቤት የምሄድ ቢሆንም ለአረፋ በዓል ሄጄ አላውቅም። እንደው ብር ተብሎ ቢኬድ አሁን የምመኘው በአረፋ በዓል እናቴ እቅፍ ውስጥ መገኘትን ነው።

ለምህረት አስቻለው እንደነገረቻት

ካለሁበት 27፡ 'እንጀራ ከበላሁ ዓመት አልፎኛል'

ካለሁበት 28፡ "ያደግኩበት አካባቢና የሰፈሬ ልጆች በጣም ይናፍቁኛል"

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ